ዘመቻ አንድነት በሚል ስያሜ በአማራ ክልል ትንኮሳ ለመፈፀም የሞከረው ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው ፅንፈኛ ተደመሰሰ - ኢዜአ አማርኛ
ዘመቻ አንድነት በሚል ስያሜ በአማራ ክልል ትንኮሳ ለመፈፀም የሞከረው ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው ፅንፈኛ ተደመሰሰ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2017(ኢዜአ)፦ዘመቻ አንድነት በሚል ስያሜ በተለያዩ የአማራ ክልል የዞን ወረዳዎች ትንኮሳ ለመፈፀም የሞከረው ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው ፅንፈኛ ቡድን መደምሰሱን መከላከያ ሰራዊት ገለጸ።
ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በብርጋዲየር ጄኔራል ምግበ ሀይለና ግብረ አበሮቹ አደራጅነትና አይዞህ ባይነት ዘመቻ አንድነት በሚል ስያሜ በተለያዩ የአማራ ክልል የዞን ወረዳዎች ትንኮሳ ለመፈፀም የሞከረው ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው ፅንፈኛው ቡድን ተደምስሷል።
ብርጋዲየር ጄኔራል ምግበይ ዕድሜ ልኩን በታሪኩ ግጭት እየጠመቀ የትግራይን ሕዝብ ወደ ጦርነት በማስገባት ያለ ምንም ወታደራዊ ዕውቀት ወጣቱን ወደ እሳት አስገብቶ የማስፈጀት ታሪክ ያለው ፀረ ሠላምና ፀረ ልማት አራማጅ ነው ብሏል መረጃው።
ውጊያ ከብዶት የሸሸውን ወጣት ለምን ሸሸህ በሚል ሰበብ በጅምላ የመረሸን ልምድ ያለውና ያለዕውቀት የትግራይን ወጣቶች ደም ሲመጥ የቆየ መሆኑ ሳያንሰው፤ አሁን ላይም የፅንፈኛው መሪዎች ነን ባዮች አማካኝነት የሠላም ፈላጊውን የአማራን ወጣት ሕይወት ለመቅጠፍ እንቅስቃሴ የጀመረ መሆኑ ታውቋል ብሏልም መረጃው።
ባለፈው ጊዜ በነበረው የሰሜኑ ጦርነት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶችን እየረሸነ እያስረሸነ የፈጀ የጥቁር ታሪክ ፀሃፊነቱ ሳያንስ፤ አሁን ላይም መሠል ድርጊት ለመፈፀም እየተንቀሳቀሰ ነው ተብሏል፡፡
ምዕራብ ትግራይን አስመልሳለሁ በሚል እሳቤ ሁለት ጊዜ የፌዴራል መንግስት ሠራዊትን ለማጥቃት ሞክሮ፤ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ያስበላ ውጊያ እምቢ ሲለው የራሱን ታጣቂዎች ረሽኖና ገድሎ ውጊያው ሳይሳካለት አከርካሪው ተመትቶ ሸሽቷል ብሏል መከላከያ ሠራዊት።
ምግበይ ኃይለ ዘረፋና ሌብነት የተካነበት መደበኛ ሥራው ነው ያለው የመከላከያ ሠራዊት መረጃ፤ በአሁኑ ጊዜ የትግራይን ወርቅ እየዘረፈ በኤርትራ በኩል አድርጎ እየሸጠ ይገኛል ሲል ገልጿል።
በኢህአዴግ ዘመን በዘረፋና ሌብነት ታዋቂ የነበረ ብቻ ሳይሆን፤ በሰረቀውና በዘረፈው ገንዘብ አዲስ አበባ ላይ ፎቆችን የደረደረ አለፍ ሲልም ዱባይ ላይ ፎቆችን ለመሥራት በቅርብ ጊዜ የተዋዋለ ስለመሆኑ በሶሻል ሚዲያ ሲነገር ቆይቷል ነው የተባለው።
በጦርነት ከቀቀለው ወጣት በተጨማሪ የረሸናቸው በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በመኖራቸው፤ ትግራይ ሰላም እንድትሆን ከቶውንም አይፈቅድም ሲል መከላከያ ሠራዊት ገልጿል ፡፡
ምክንያቱ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን ይጠይቀኛል የሚል ስጋት አንደኛው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ እያደረገ ያለው የወርቅ ዘረፋ እንዳይጋለጥበት በማሠብ መሆኑም ተገልጿል።
በሌላ በኩል ምግበይ ኃይለ የፕሪቶሪያን ስምምነት እንዲፈርስ እንዳይሳካ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ያለ ከመሆኑም በላይ፤ የጊዜያዊ አስተዳድሩን ማህተም ለመንጠቅ እና በኃይል አፍርሶ ሥልጣን ለመያዝ የሞከረ የፀረ ሠላምና ፀረ ልማት አራማጅ ነው ብሏል መረጃው።
የሠላም ጠንቅ የሆነው ምግበይ ኃይለ ለዚህ መሰሪ ተግባሩ ጽንፈኛውን ኃይል እንደ ተባባሪነት በመጠቀም በራሱ ክልል ላይ ያልተገባ ውድመት እንዲፈፅም አዝዞታል ነው ያለው።
ነገር ግን ዘመቻ አንድነት በሚል ስያሜ ፅንፈኛውን አስተባብሮ በጀመረው ትንኮሳ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሷበታል ይላል የመከላከያ ሠራዊት መረጃ።
በደቡብ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በሰሜን ጎጃም፣ በምስራቅ ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም እንዲሁም በሰሜን ወሎ የምግበይ ኃይለ ተላላኪ ፅንፈኞች በለኮሱት እሳት ተለብልበዋል ተብሏል።
በነዚህ ሁለት ቀናት ብቻም 317 የተገደለ፣ 41 የተማረከ፣ 125 የቆሰለ፣ 27 እጅ የሠጠ፣ 51 በምህረት የገባ፣ 15 መረጃ አቀባይ የተያዘ፣ በድምሩ 576 የሠው ኪሳራ እንደደረሰበትም መረጃው ያመለክታል።
እንዲሁም 1 መትረየስ፣ 119 ክላሽ፣ 46 ኋላቀር መሣሪያ፣ 8 ሽጉጥ፣ 22 ቦምብ፣ 2 ሺህ 290 የተለያዩ ዓይነት ተተኳሾች፣ 28 ትጥቅ፣ የመገናኛ ራዲዮ፣ ተሽከርካሪ፣ ባጃጅ፣ ሞተር ሳይክል እና ሌሎች ቁሶችም በሠራዊታችን ቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል።
ይህ በምግበይ ኃይለ እና በግብረ አበሮቹ አይዞህ ባይነት የተጋለበው ፅንፈኛ ቡድን፤ በዚህ ልክ ኪሳራ የደረሰበት ሲሆን በሕይወት የተረፈው የትም የተበታተነ መሆኑ ተገልጿል።