የመንግሥት ሠራተኛው ታማኝ የህዝብ አገልጋይ መሆን አለበት- የወልዲያ ከተማ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥት ሠራተኛው ታማኝ የህዝብ አገልጋይ መሆን አለበት- የወልዲያ ከተማ አስተዳደር
ወልዲያ፤መጋቢት 12/2017(ኢዜአ)፦የመንግሥት ሠራተኛው ታማኝ የህዝብ አገልጋይ በመሆን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ መሪ ተዋናይ መሆን እንዳለበት የወልዲያ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የወልዲያ ከተማ አስተዳደር በመምሪያዎች የበጀት አመቱ ስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም አስመልክቶ ዛሬ በወልዲያ ከተማ ከመንግስት ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል።
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ህዝቡ የሚያነሳውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍታት ቀሪ ተግዳሮት ነው።
ህብረተሰቡ በማዘጋጃ፣ በንግዱ ዘርፍ፣ በከተማ መሬት አስተዳደር፣ በትራንስፖርት፣ በሆስፒታልና ሌሎች ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አሁንም ቅሬታ ያለበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
"የመንግስት ሰራተኞች በጀት ዓመቱ ቀሪ ወራቶች ታማኝ ህዝባዊ አገልጋይነታችሁን በበለጠ በተግባር በማረጋገጥ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ መሪ ተዋናይ ልትሆኑ ይገባል " ብለዋል።
የወልዲያ ከተማ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ አስናቀች ኃይሌ በበኩላቸው እንዳሉት የመልካም አስተዳደር ስኬት የሚለካው ሠራተኛው በሚያስመዘግበው የስራ ውጤት ነው።
"ባለፉት ወራቶች የተከናወኑ ተግባራት ከህዝቡ ጥያቄና ከከተማው የመልማት ፍላጎት አንጻር ሲታይ ገና ብዙ የሚቀር መሆኑን በመገንዘብ ለቀጣይ ስራ በቁርጠኝነት መሰለፍ ይገባል" ብለዋል ።
"መምሪያዎች በስራቸው ባለው ሰራተኛ የስራ አፈጻጸም ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ህዝቡን እንዲያገለግሉ ማድረግ አለባቸው" ሲሉም አስገንዝበዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የመድረኩ ተሳታፊ ሠራተኞች በበኩላቸው "የተሠጠን ህዝብን የማገልገል ኃላፊነት የኑሮ ዋስትናችን ጭምር በመሆኑ ጠንክረንና ትርጉም ሰጥተን እንሠራለን" ብለዋል።
በመድረኩም የተሻለ አፈጻጸም ላሳዩ መምሪያዎች የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።