የሎጅስቲክስ አገልግሎት ዘርፍን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሎጅስቲክስ አገልግሎት ዘርፍን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 12/2017(ኢዜአ)፡-መንግስት የሎጅስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ ለማሳደግ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዴንጌ ቦሩ ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታው ተቀማጭነቱን ጀርመን ካደረገው የለርን ሎጂስቲክስ ባይ ኩን ፋውንዴሽን ከተሰኘ ድርጅት ተወካዮች ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ድርጅቱ በስልጠና እና ስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ላይ በአጋርነት የሚሰራ ነው።
ሁለቱ ወገኖች የሎጂስቲክስ አገልግሎት ባለሙያዎች ስልጠና፣የስልጠና ካሪኩለም ዝግጅት እና መሰል ስራዎች ላይ መክረዋል።
አቶ ደንጌ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አቅም በመገንባት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን የአፍሪካ ብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ውጥን እንዲሆን ቁልፍ የሆነውን የሎጂስቲክስ አገልግሎት የማሳደግ ስራ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው አመልክተዋል።
በሎጂስቲክስ ዘርፍ ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ሚኒስቴሩ ከድርጅቱ ጋር በትብበር መስራት እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።
መንግስት የሎጂስቲክስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከትምህርት ተቋማት ጋር ተቀናጅተው በመስራት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
የለርን ሎጂስቲክስ ተወካዮች በበኩላቸው ድርጅቱ በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያለውን የሎጂስቲክስ አገልግሎት ማሻሻል ላይ ውጤታማ ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል።
ተቋሙ ከሚኒስቴሩ ጋር በመተባበር የሎጂስቲክስ ባለሙያዎችን አቅም ለማሳደግ እንደሚሻም መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።