ኢትዮጵያ የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ ለቀጣናው ዘላቂ ልማት አሻራዋን እያሳረፈች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ ለቀጣናው ዘላቂ ልማት አሻራዋን እያሳረፈች ነው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 12/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግና ድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሶችን በማልማት ለቀጣናው ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃና ልማት አሻራዋን እያሳረፈች መሆኗን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።
14 ኛው አለም አቀፉ የደን ቀን "ደንና ምግብ" በሚል መሪ ሀሳብ ተከብሯል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በመሬት አቀማመጥ፣በተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ተስማሚ የአየር ንብረት የታደለች ሀገር ናት።
በብዝኃ ህይወት ስብጥርም በዓለም ተጠቃሽ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቁመዋል።
ደን ዘላቂ ምርታማነትን ለማረጋገጥ የማይተካ አስተዋጽኦ ቢኖረውም ከዚህ ቀደም በነበሩ ጊዜያት ደንን መሰረት ባላደረገ የኢኮኖሚ ዘይቤ ምክንያት የከፋ የደን መመናመን እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ይህንን የሚያስተካክል ፖሊሲ ቀርጻ በመተግበር ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ በፍራፍሬ ልማት የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ መሳሪያ መሆኑን አንስተዋል።
በተጨማሪም ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑን እና በስራ እድል ፈጠራም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
ለ2017 የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እስካሁን 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ስድስት አመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከ 40 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ ዝርያና ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በመትከል የደን ሽፋንን በጉልህ ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።
በቅርቡ በመንግስት የጸደቀው የአረንጓዴ አሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ አዋጅ በኢትዮጵያ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የተጀመሩ ሥራዎችን የሚያሳካ ነው ብለዋል።
መንግስት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት መስጠቱን አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ የበርካታ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች መገኛ በመሆኗ የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረግ ለቀጣናው ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃና ልማት አሻራዋን እያሳረፈች መሆኗን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም በበኩላቸው፥ደን በዓለማችን ለ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የህብረተሰብ ክፍል የኑሮ መሰረት ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የደን ሀብትን ለማስፋት፣ምርታማነትን ለማረጋገጥ እና ብዝኃ ህይወትን ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን ጠቅሰው፥ ዓመታዊ የደን ጭፍጨፋም በከፍተኛ መጠን እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ደን ልማትም ዘርፉን በእውቀት እና በክህሎት ለመምራት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።