ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ሰላማዊ ግንኙነት አብሮ የማደግ ፍላጎቷ ማሳያ ነው -አምባሳደር ዲና ሙፍቲ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ሰላማዊ ግንኙነት አብሮ የማደግ ፍላጎቷ ማሳያ ነው -አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 12/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ሰላማዊ ግንኙነት አብሮ የማደግ ፍላጎቷ ማሳያ ነው ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፥ትናንት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር የመልማት ፍላጎቷን በተግባር ማሳየቷን ገልጸዋል።
የባህር በር ጥያቄዋ የህልውና ጉዳይና በመርህ ላይ የመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጦር የሚያማዝዝ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
በዚህ ጉዳይ ከማንም ጋር ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌላት በአፅንኦት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የልማትና የብልጽግና ህልሟን እውን ለማድረግ ከሀገራት ጋር በትብብር ትሰራለች ብለዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፥ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ሰላማዊ ግንኙነት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፣መንግስት ባለፉት ዓመታት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ሰላማዊና በትብብር ላይ የተመሰረተ ለማድረግ ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ ናቸው።
ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ጭምር ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት በመስጠት በሁሉም ዘርፍ ትብብሯን ለማሳደግ እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል።
በቅርቡ ከሶማሊያ ጋር የነበረውን መጠራጠር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተደረገው ጥረትም የዚህ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር እየሰራች ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፥ ይህም ሀገራቱ መተማመንን በማጎልበት በጋራ እንዲያድጉ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ሰላማዊ ግንኙነት የፈጠሩ ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን የማጠናከርና በጋራ የመልማት ዕድላቸው የተሻለ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ባስተናገደቻቸው አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች እንዲሁም በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን መድረኮች በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ማሳየቷንም ገልጸዋል።
ፍላጎቷን በሰጥቶ መቀበል መርህ እንጂ በጦርነት ማሳካት እንደማትፈልግና በአንዳንድ ሀገራት ውስጥ ያሉ ግጭቶች በውይይት እንዲፈቱ ሚናዋን እንደምትወጣም አንስተዋል።