ጠንካራ የካፒታል ገበያ ሥርዓት ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው - የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ - ኢዜአ አማርኛ
ጠንካራ የካፒታል ገበያ ሥርዓት ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው - የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 12/2017(ኢዜአ)፦ጠንካራ የካፒታል ገበያ ሥርዓት ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዥና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከሚሰጣቸው አስራ አምስት አይነት የአገልግሎት ፈቃድ አይነቶች በኢንቨስትመንት ባንኪንግ 25 ሚሊየን ብር፣ የሰነደ ሙዓለንዋይ ገበያ አከናዋኝ 10 ሚሊየን ብር እና የሰነደ ሙዓለንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪነት 500 ሺህ ብር የካፒታል መጠን ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣንም መስፈርቱን ላሟሉ አምስት አዳዲስ ድርጅቶች የኢንቨስትመንት ባንክ፣ የሰነደ ሙዓለንዋይ ገበያ አከናዋኝና የሰነደ ሙዓለንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪ ፈቃድ መስጠቱን አስታውቋል።
በሥነ-ስርዓቱ ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዥ እና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የቦርድ ሰብሳቢ ማሞ ምህረቱ፥ የዳበረና ጠንካራ የካፒታል ገበያ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ብልጽግና አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ሀገራዊ ቁጠባን በማሳደግ በሚፈጥረው የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ለሀገር ዕድገትና ሥራ ፈጣሪ ቁልፍ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ለማሳለጥ የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የካፒታል ገበያ ባደገበት ሀገር ኩባንያዎች አክሲዮንና የብድር ሰነዶችን በመሸጥ ምርታማነትን ለሚያሳድጉ ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍ ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
በሌላ መልኩም የካፒታል ገበያ ለህብረተሰቡ አማራጭ የገንዘብ ቁጠባ ዘዴን በማቅረብ ሀገራዊ የፋይናንስ አቅምን ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በዚህም የመንግስትን፣የባንኮችን፣የአምራቾችና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማሳደግ የሀገርን የክፍያ ሚዛን በማስተካከል ለማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ፥ ባለስልጣኑ ገበያውን ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ በማስገባት የሀገርን ኢንቨስትመንት የሚያግዝ ሥርዓት እየፈጠረ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢንቨስትመንት ባንክ፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ አከናዋኝ እና የሰነደ ሙዓለንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ ድርጅቶች ፈቃድ መስጠቱን ገልጸዋል።
እስካሁን ፈቃድ የተሰጣቸው የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ቁጥር ዛሬ ፈቃድ የተሰጣቸውን ጨምሮ ዘጠኝ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶችም አገልግሎት አሰጣጣቸው ጠንካራ፣ ግልጽ፣ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን የሚያሳዩ መሆናቸውን የማረጋገጥ ሥራ መሠራቱን አንስተዋል።
ዛሬ ለሲቢኢ ካፒታል አ.ማ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ ለወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ አ.ማ፣ ለኢትዮ-ፊደሊቲ ሴኩሪቲስ አ.ማ የሰነደ ሙዓለንዋይ ገበያ አከናዋኝ፣ ለኤች ኤስ ቲ ኢንቨስትመንት አድቫይዘሪ ሰርቪስ ኃ.የተ.የግ.ማ የሰነደ ሙዓለንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪና ለኢኩዥን የሰነደ ሙዓለንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ ኃ.የተ.የግ.ማ የሰነደ ሙዓለንዋይ ኢንቨስትመንት አማካሪ ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል።
ባንኮችና ሌሎች ኩባንያዎችም የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለንዋይ ገበያ የሚሰጣቸውን አስራ አምስት አይነት የአገልግሎት ፈቃዶችን በመውሰድ ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።