በጋምቤላ ክልል የኮደርስ ዲጂታል ስልጠና አፈጻጸምን ለማጠናከር በትኩረት መስራት ይገባል - ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የኮደርስ ዲጂታል ስልጠና አፈጻጸምን ለማጠናከር በትኩረት መስራት ይገባል - ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2017(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል በኮደርስ ዲጂታል ስልጠና የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን(ዶ/ር) አስገነዘቡ።
የክልሉ የ5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ፕሮግራም አፈጻጸም ተገምግሟል።
ፕሮግራሙ በጋምቤላ ክልል መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን(ዶ/ር) በክልሉ በሶስት ዓመት ውስጥ 47 ሺህ 287 ሰዎች ስልጠናውን እንዲወስዱ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ዓመት 11ሺህ 822 ተሳታፊዎች ስልጠናውን እንዲከታተሉ ግብ መቀመጡንም አመልክተዋል።
ይሁንና አፈጻጸሙ በሚፈለገው ደረጃ ላይ እንደማይገኝና ይህንን ለማሻሻል አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በቀጣይ ሰፊ ቅስቀሳና ንቅናቄ በማድረግ፣ የቅንጅት አሰራርንና ክትትልን በማጠናከር እንዲሁም በግንዛቤ ፈጠራ በተሻለ መልኩ ማከናወን እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።