ቀጥታ፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን 710 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ በርበሬ ምርት ተሰበሰበ

ጭሮ ፤መጋቢት 12/ 2017(ኢዜአ)፡-በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በዚህ አመት በበርበሬ ከለማው መሬት 710 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የቡና እና ቅመማ ቅመም ልማት ቡድን አስተባባሪ አቶ ኦሉማ በዳኔ ለኢዜአ እንደገለጹት ምርቱ የተሰበሰበው በዞኑ 15 ወረዳዎች በልማቱ ከተሸፈነው 43 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ነው፡፡

በዚህ አመት የተሰበሰበው ምርት መጠን ካለፈው አመት ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ መጨመሩን ገልጸው የለማው መሬት መጠንም ከስድስት ሺህ ሄክታር በላይ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል፡፡ 


 

በልማቱ በወረዳዎቹ የሚገኙ ከ35 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸቸውንም ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ ከቀዳሚው አመት የተሻለ ምርት መጠን ሊገኝ የቻለው በቂ የዝናብ ስርጭት በመኖሩ አርሶ አደሩ በምርት እንክብካቤ የበለጠ ትኩረት በመስጠቱና ተጨማሪ መሬት በልማቱ በመሸፈኑ ነው ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮች በባለሙያዎች በመታገዝ በምርት እንክብካቤ በትኩረት በመሳተፋቸው ዘንድሮ በሄክታር ይገኝ የነበረው ምርታማነት በአማካይ ከ16 ኩንታል ወደ 22 ኩንታል ሊያድግ እንደቻለ አብራርተዋል፡፡

የበርበሬ ልማቱ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ቢለማም በጭሮ፣ ቦኬ፣ ሀዊ ጉዲና፣ ገመቺስ፣ ዳሮ ለቡ፣ ሀብሮ እና ኦዳ ቡልቱም ወረዳዎች  ልማቱ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚከናወን አመልክተዋል፡፡ 

በጭሮ ወረዳ ነጀባስ ቀበሌ በልማቱ የተሰማሩት ወይዘሮ ኢፍቱ አልይ በሰጡት አስተያየት በዚህ አመት ከዚህ ቀደም በዋናነት ከሚያለሙት የእህል ሰብል ምርት በተጨማሪ ማሳቸውን ለበርበሬ ልማት እያዋሉ ነው፡፡

በዚህ አመት ሩብ ሄክታር ከሚሆን ማሳ ላይ ስምንት ኩንታል ምርት ማግኘታውን ገልጸው በዚህም ገቢያቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ከወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ምርጥ የበርበሬ ዘር በነጻ በማግኘታቸው ከማሳቸው ግማሽ ያህሉን በበርበሬ ልማት በመሸፈን 12 ኩንታል እንዳገኙ የተናገሩት ደግሞ አርሶአደር ኢብራሂም ጀማል ናቸው፡፡

በቀጣዩ ክረምት ልማቱን በማሳ ላይ በማስፋፋት ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ማቀዳቸውንም ተናግረዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም