ቀጥታ፡

ለ2017 የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር እስካሁን 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል - ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2017(ኢዜአ)፡- ለ2017 የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር እስካሁን 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።

14ኛው አለም አቀፍ የደን ቀን "ደንና ምግብ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ነው።

በመርሀ-ግብሩ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሙባረክ ኤልያስ፣ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ፣ የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም እንዲሁም የፌደራል እና የክልል የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ በመሬት አቀማመጥ፣ በተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ተስማሚ የአየር ንብረት የታደለች ሀገር ናት።

በብዝኃ ህይወት ስብጥርም በዓለም ተጠቃሽ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቁመዋል።


 

ደን ዘላቂ ምርታማነትን ለማረጋገጥ የማይተካ አስተዋጽኦ እንዳለው አመላክተዋል።

ከዚህ ቀደም በነበሩ ጊዜያት ደንን መሰረት ባላደረገ የኢኮኖሚ ዘይቤ ምክንያት የከፋ የደን መመናመን እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ይህንን የሚያስተካክል ፖሊሲ ቀርጻ በመተግበር ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ በፍራፍሬ ልማት የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ መሳሪያ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆኑንና በስራ እድል ፈጠራም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።

ለ2017 የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እስካሁን 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

መንግስት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ለተፈጥሮ ጥበቃ እና ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት መስጠቱን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም በበኩላቸው ደን በዓለማችን ለ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የህብረተሰብ ክፍል የኑሮ መሰረት ነው ብለዋል።

እንዲሁም በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ሀብት መሆኑን ጠቅሰው፤ በደን ላይ የሚደርስ ጉዳት ዘላቂ ልማትን ወደ ኋላ የሚቀለብስ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ምርታማነትን ለማረጋገጥ እና ብዝኃ ህይወትን ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ደን ልማትም ዘርፉን በእውቀት እና በክህሎት ለመምራት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም