በክልሉ የተሟላ የግብርና ፓኬጅን በመተግበር የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው--ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተሟላ የግብርና ፓኬጅን በመተግበር የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው--ቢሮው
ባህርዳር ፤መጋቢት 12/2017 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የተሟላ የግብርና ፓኬጅን በመተግበር የሰብል ምርታማነትን በላቀ ደረጃ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው 2017/18 የምርት ዘመን የመኸር ሰብል ልማት ፓኬጅ የአሰልጣኞች ስልጠናና የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለፁት ለመጪው የመኸር ምርት 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን ወደ ስራ ተገብቷል።
በመኸር ሰብል ልማቱ አርሶ አደሩ የግብርና ፓኬጅን በአግባቡና በተሟላ ሁኔታ በመተግበር ለማግኘት የታቀደውን 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ግብ ለማሳካት መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።
ክልሉ 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እያስገባ መሆኑን ጠቁመው ቀድሞ የደረሰውን ለአርሶ አደሩ የማሰራጨት ተግባርን ወረዳዎች እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
አርሶ አደሩም የመስመርና የኩታ ገጠም አሰራርን ተጠቅሞ በመዝራት እንዲሁም የምርት ማሳደጊያ ግብዓትን በአግባቡ በመጠቀም ምርታማነቱን ማሳደግ እንዳለበት ገልጸዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችና አመራር አባላት ክልሉን ከድህነት ለማላቀቅና የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችል ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንዳለባቸውም አሳሰበዋል።
የስልጠናው ዓላማም በየቀበሌው ለሚገኙ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች አዳዲስ የግብርና ፓኬጆች ላይ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል አቅምን ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአፈርና ውሃ ምርምር ዳይሬክተር ተስፋዬ ፈይሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በአሲድ የተጠቃ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት እያደገ እንዲመጣ ምክንያት መሆኑን ጠቁመው አርሶ አደሩ አሲዳማ መሬትን ለማከም የአፈር ለምነትና ጤንነት ለመጠበቅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ላይ ማተኮር አለበት ብለዋል።
የአፈር ለምነትን ለማሻሻል በበጋ እርሻን ደጋግሞ ማረስ አንዱ ፓኬጅ ነው ያሉት ደግሞ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባንጃ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አለማየሁ ሙሉጌታ ናቸው።
ለዚህም በወረዳው ለመጪው የምርት ዘመን በተለያዩ ሰብሎች ከሚለማው ሰባት ሺህ 128 ሄክታር መሬት እስካሁን 68 በመቶ የሚሆነው ከአንድ እስከ ሶስት ጊዜ መታረሱን ገልጸዋል።
ለሶስት ቀናት በሚቆየው የአሰልጣኞች ስልጠናና የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ላይም ከምዕራብ አማራ ዞኖችና ወረዳዎች፣ ከክልሉ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የተውጣጡ ባለሙያዎችና አጋር አካላት እየተሳተፉ ነው።