ቀጥታ፡

ውሃ እና ውሃ አዘል መሬቶችን ከብክለትና ከጉዳት በመጠበቅ ለዘላቂ ጥቅም ለማዋል በቅንጅት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2017(ኢዜአ)፡- ውሃ እና ውሃ አዘል መሬቶችን ከብክለትና ከጉዳት በመከላከል ለዘላቂ ጥቅም ለማዋል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ብርቅዬና ዓይነተ ብዙ ለሆኑ የብዝሃ-ሕይወት ሃብቶች ምቹና ተስማሚ ሥነ-ምህዳር አላት።

ውሃና ውሃ አዘል መሬቶች የበርካታ ብዝሃ ህይወት መኖሪያ እንደመሆናቸው ሃብቱን በአግባቡ መያዝ፣ መጠበቅና መንከባከብ ወሳኝ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መለሰ ማርዮ(ዶ/ር) እንዳሉት ውሃ አዘል መሬቶች ብዝሃ ሕይወትን ከአየር ንብረት ለውጥ፣ ከብክለት፣ ከጎርፍና ከድርቅ በመከላከል ረገድ ጉልህ ሚና አላቸው።

ለአካባቢ ስነ-ምህዳር መጠበቅም ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው በመሆኑ በአግባቡ መጠበቅና መንከባከብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

ረግረጋማ አካባቢዎች በከተሞችና በእርሻ መሬቶች መስፋፋት፣ በብክለት፣ በመጤ የእፅዋት ዝርያዎች መስፋፋት ሊደርቁ ብሎም ሊጠፉ እንደሚችሉ አንስተዋል።

በኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የውሃ አካላትና ውሃ አዘል መሬቶች አጠቃቀም ቁጥጥር ዴስክ ሃላፊ ዘሪሁን መንገሻ እንዳሉት ውሃ አዘል መሬቶችን በተመለከተ ራሱን የቻለ ተቋም አለመኖር በርካታ ጥፋቶች ሲከሰቱ እንደነበር ተናግርዋል።

ለውሃ አዘል መሬቶች አጠቃቀም ራሱን የቻለ የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ችግሩን ለመከላካል የሚሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎት መቆየቱን የጠቀሱት ደግሞ ዶክተር መለሰ ማርዮ ናቸው።

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቻው ባለስልጣኑ በህግ ከተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት መካከል ዘላቂ የአካባቢ አያያዝ ስርዓት ቁጥጥርን ማጎልበት አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

የአካባቢ ቁጥጥር ከሚካሄድባቸው ሀብቶች መካከል ውሃ እና ውሃ አዘል መሬቶች ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል።

እነዚህን ሃብቶች ከብክለትና ከጉዳት ለመከላከልና ለዘላቂ ጥቅም ለማዋል ከባለደርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በተጨማሪም የውሃ አካላት አጠቃቀም ላይ የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በውሃ አዘል መሬቶች የተሸፈነ ሰፊ መሬት እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም