ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ እንደምትችል ያሳየና የአብሮነታችን መገለጫ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ እንደምትችል ያሳየና የአብሮነታችን መገለጫ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2017(ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ እንደምትችል ያሳየና የአብሮነታችን መገለጫ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ስድስተኛው ዙር የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ትናንት ተካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የፌዴራል መንግስት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት አፈፃፀምን መነሻ በማድረግ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በእለቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ ከተዳሰሱ ጉዳዮች መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ አፈጻጸም ይገኝበታል።
ጉዳዩን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የህዳሴ ግድብ ሪቫንን እንቆርጣለን ሲሉ ለምክር ቤቱ አብስረዋል።
ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ መቻልን ያሳየችበት እና ስህተታችንን ያረምንበት ጭምር ነው ሲሉ መግለጻቸውም እንዲሁ።
ግድቡን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች እንደገለጹት የህዳሴ ግድብ ግንባታን በሚመለከት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላለፈው መልእክት ተስፋ ሰጪና በእጅጉ የሚያስደስት ነው።
በተጨማሪም የኢትዮጵያን ተደማጭነት ከፍ የሚያደርግ፣ እድገቷን የሚያፋጥንና ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅምን የሚፈጥር ስለመሆኑም አንስተዋል።
አቶ ዮናስ ወልደየስ የተባሉ የመዲናዋ ነዋሪ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጋራ የተሰለፉበትና አንድነታቸውን ያረጋገጡበት ዳግማዊ አድዋ ነው ብለዋል።
አቶ ታሪኩ ፍቅሬ በበኩላቸው ህዳሴ ግድብ ለትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ ሃብትና ለሌላ ተጨማሪ ልማት የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸዋል።
ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን አይችሉም የሚለውን አስተሳሰብ የቀለበሰና የአብሮነት መገለጫ ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ እመቤት ውድነህ ናቸው፡፡
ህዳሴ ግድብ በመተባበርና አብሮነትን በማጽናት የማይቻል ነገር እንደሌለ የሚያሳይ የአንድነት ተምሳሌት መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ኢትዮጵያውያን ከህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ሊያሳኩት የሚገባ ትልቅ ፕሮጀክት ሊሆን አንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።