ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ትጫወታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ትጫወታለች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2017 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ23ኛ የፊፋ ዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ አምስተኛ ጨዋታውን ዛሬ ከግብጽ አቻው ጋር ያደርጋል።
የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከሌሊቱ 6 ሰዓት ላይ በሞሮኮ ካዛብላንካ በሚገኘው ላርቢ ዛውሊ ስታዲየም ይካሄዳል።
በማጣሪያው በምድብ አንድ የምትገኘው ኢትዮጵያ በሶስት ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ተጋጣሚዋ ግብጽ በ10 ነጥብ ምድቡን እየመራች ነው።
ኢትዮጵያ በምድቧ እስከ አሁን ባደረገቻቸው አራት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ስትሸነፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥታለች።
ግብጽ ባደረገችው አራት ጨዋታ ሶስት ጊዜ ስታሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥታለች።
በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለጨዋታው የመጨረሻ ልምምዱን ጨዋታው በሚደረግበት ላርቢ ዛውሊ ስታዲየም ትናንት ማምሻውን ማድረጉን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የ39 ዓመቱ ሞሪሺየስ ዜግነት ያላቸው ፓትሪስ ሚላዛሬ የሀገራቱን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
ዋልያዎቹ በማጣሪያው ስድስተኛ የምድብ ጨዋታቸውን ሰኞ መጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ከጅቡቲ ጋር ያደርጋሉ።
ብሄራዊ ቡድኑ ከጨዋታዎቹ የተሻለ ነጥብ መሰብሰብ በማጣሪያው ለሚኖረው ቀጣይ ጉዞ በጣም ወሳኝ የሚባል ነው።
23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ እ.አ.አ በ2026 በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ጣምራ አዘጋጅነት ይካሄዳል። በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት ይሳተፋሉ።
በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ 54 የአፍሪካ ሀገራት በዘጠኝ ምድብ ተከፍለው የማጣሪያ ጨዋታ እያደረጉ ነው።
አፍሪካ በዓለም ዋንጫው 9 ሀገራት በቀጥታ ታሳትፋለች። ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረው የ5 ሀገራት ተሳትፎ እድገት አሳይቷል።
አንድ የአፍሪካ ቡድን በሌሎች አህጉራት ከሚገኙ ሀገራት ጋር በሚደረግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ካሸነፈ አህጉሪቷን የሚወክል 10ኛ ሀገር ይሆናል።