ቀጥታ፡

የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ኢትዮጵያውያን ከህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ሊያሳኩት የሚገባ ትልቅ ፕሮጀክት ነው -የምክር ቤት አባላት

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2017(ኢዜአ)፡- የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ኢትዮጵያውያን ከህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ሊያሳኩት የሚገባ ትልቅ ፕሮጀክት ሊሆን አንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመንግስትን የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት ለሆነው የግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነት መጨመር በተደረጉ ጥረቶች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል። 

ይሁንና በተለይም ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ፍላጎት ጋር በተያያዘ አሁንም ድረስ ያልተፈታ ችግር መሆኑን ነው ያስረዱት።

ለዚህም ደግሞ መንግስት ዘላቂ መፍትሄ ብሎ ያቀደው ከውጭ የሚመጣውን የአፈር ማዳበሪያ ለመተካት የማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት ነው ብለዋል። 

ይህም ደግሞ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ኢትዮጵያውያን ሊያሳኩት የሚገባ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን አመልክተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የምክር ቤት አባላትም እንደገለጹት፤ መንግስት ያቀረበው የማዳበሪያ ፋብሪካ የመገንባት እቅዱ የወቅቱን አንገብጋቢ ጥያቄ የሚመልስ ነው። 

ከውጪ ተገዝቶ የሚገባው ማዳበሪያ አርሶ አደሩ ጋር ተጓጉዞ እስኪደርስ የሚወስደው ጊዜና ወጪ ቀላል የሚባል አለመሆኑንም ነው የተናገሩት። 

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ከፈና ኢፋ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት እንዳለበት ጥያቄዎች ሲቀርቡ እንደነበር አንስተዋል።

መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የአፈር ማዳበሪያ በማስገባት ለአርሶ አደሩ በማድረሱ በግብርናው ላይ ምርትና ምርታማነት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

የማዳበሪያ ፋብሪካው ማሳካት የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት ለሆነው የግብርና ምርት የበለጠ እንዲጨምርና በተለያዩ ምክንያቶች የሚስተዋለውን የዋጋ ጭማሪ ለመቀነስ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።


 

ሌላው የምክር ቤት አባል ዓለሙ ጎንፋ ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ በመገንባት በራስ ማምረት  የኢኮኖሚ ዕድገቷን የበለጠ ያፋጥናል ነው ያሉት። 

ለማዳበሪያ ግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረትና ለሌላ ልማት ለማዋል የፋብሪካው መገንባት ትልቅ ጠቀሜታ አንዳለውም ገልጸዋል። 

የመንግስት እቅድ ጊዜውን የዋጀ በመሆኑ የፋብሪካው ግንባታ እንዲሳካ በቁጭት መነሳት ያስፈልጋል ብለዋል። 

መንግስት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል የያዘው እቅድ ለማሳካት በውጭ ምንዛሬ እየተገዛ የሚገባውን የአፈር ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ሲቻል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የምክር ቤቱ አባል ኑራዝማን ጅብሪል(ዶ/ር) ናቸው። 


 

የማዳበሪያ ፋብሪካው ግንባታ ኢትዮጵያውያን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ቀጥሎ በጋራ ልምናሳካው የሚገባ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ሲሉም ነው የተናገሩት። 

ለፋብሪካው ግንባታ እውን መሆን የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የድርሻውን ለማበርከት መዘጋጀት አለበት ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም