ፌስቲቫሉ ሀገር በቀል እሴቶችን በማስተዋወቅ በቀጣናው ሀገራት አንድነትን የሚያጠናክር ነው - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ - ኢዜአ አማርኛ
ፌስቲቫሉ ሀገር በቀል እሴቶችን በማስተዋወቅ በቀጣናው ሀገራት አንድነትን የሚያጠናክር ነው - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2017(ኢዜአ)፡- የምሥራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባሕል ፌስቲቫል ሀገር በቀል እሴቶችን በማስተዋወቅ በቀጣናው ሀገራት መካከል ትብብርንና አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ፡፡
2ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባሕል ፌስቲቫል “ጥበባትና ባህል ለቀጣናዊ ትብብር" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው፡፡
በመክፈቻ መርሀ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ የጥበባና ባህል ሚኒስትሮች፣ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎችና የባህል ቡድኖች ተገኝተዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በዚሁ ወቅት፤ ከቀጣናው ሀገራት ለመጡ የፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች ወደ ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ እንኳን በደህና መጣችሁ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ይሄው ፌስቲቫል የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ባህላዊ ምርቶችና አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባህልና ጥበብ የሰው ልጆች አንጡራ ሀብቶች መሆናቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፤ ድንበር አልባ በመሆኑ በሰዎች ዘንድ መስተጋብርን በመፍጠር ለትብብርና አንድነት መሰረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰፊ የባህልና የቋንቋ ትስስር ያለው መሆኑን ገልጸው፤ የኪነ ጥበብና ስነ ጥበብ ትሩፋቶችን ማህበረሰቡን ለመጥቀም አጋዥ ይሆናል ብለዋል፡፡
ፌስቲቫሉ ማህበራዊ፣ ፖቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸው፤ የተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከኢትዮጵያም የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የባህልና ኪነ ጥበባት ቡድኖች እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
ፌስቲቫሉ ሀገር በቀል እውቀቶችን የሚያሳድጉ የኪነጥበብና የፈጠራ ሥራዎች ሀገራትን የሚያስተሳስሩና የሚያቀራርቡ ትዕይንቶች የሚቀርቡበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡