የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት አስተማማኝ የሃይል አማራጭ ማግኘት ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት አስተማማኝ የሃይል አማራጭ ማግኘት ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2017(ኢዜአ)፦ የ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳን ለማሳካት በተመጣጣኝ ዋጋ፣ አስተማማኝ በሆነ መንገድ ዘመናዊ ሃይል ማግኘት ወሳኝ መሆኑን በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በብራዚል ዋና ከተማ ብራዚሊያ እየተካሔደ ባለውየብሪክስ ከፍተኛ የኢነርጂ ስብሰባ ላይ እየተሳተፈች ነው።
አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር በብሪክስ መድረክ ውስጥ ያለውን ትብብር በማጠናከር፣ ለፕላኔታችን ቀጣይነት ያለው እና የበለፀገ የወደፊት ሁኔታን ለማረጋገጥ የኢነርጂ ደህንነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
በማያያዝም የ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳን ለማሳካት በተመጣጣኝ ዋጋ፣ አስተማማኝ በሆነ መንገድ፣ዘላቂና ዘመናዊ ሃይል ማግኘት ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት የረዥም ጊዜ ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ስትራቴጂን ጨምሮ፣ ሌሎች ሀገራዊ እቅዶችን እና ስትራቴጂዎችን መሰረት አድርጎ የፈፀማቸውን ውጤታማ ተግባራት አንስተዋል።
በተጨማሪም በስብሰባው አምባሳደር ልዑልሰገድ ኢትዮጵያ ንፁህ እና ዘላቂነት ያለው ኢነርጂ ለማረጋገጥ እና ለማስቀጠል፣ የኢነርጂ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት የሀገሪቱን የኃይል ፍላጎት ለማሟላትና ክልላዊ ትብብርንና ውህደትን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
በብሪክስ መድረክ ውስጥ የኢነርጂ ትብብርን ለማጠናከር ምርጥ ተሞክሮዎች፣ ልምዶች እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ጅምሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለቡድኑ አባል አገራት ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።