የኢትዮጵያን እድገት እና ልማት የሚያፋጥኑ የምርምር ስራዎችን የመጠቀም አቅም ማሳደግ ይገባል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን እድገት እና ልማት የሚያፋጥኑ የምርምር ስራዎችን የመጠቀም አቅም ማጠናከር እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኦስትሪያ ከሚገኘው "International Institute for Applied Systems Analysis" ተቋም ጋር በበይነ መረብ ውይይት አድርጓል።

ውይይቱ የኢትዮጵያን ሀገራዊ አጀንዳ የሚደግፉ የጋራ ምርምር፣ የዕውቀት ሽግግር እና የአቅም ግንባታ ጥረቶች እድሎችን ለመለየት፣ ግንኙነት ለማጠናከርና ቀጣይ እርምጃዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ እድገትንና ልማትን ለማፋጠን በምርምር የተደገፈ ኢንቨስትመንት እና አዳዲስ ፈጠራዎችን ወደ ገበያ ለማሸጋገር እየሰራች እንደሆነ ገልፀዋል።

በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ክልላዊ አባል ሀገራት ንቁ ተሳታፊ መሆኗንም ተናግረዋል።

የ10 ዓመት የልማት እቅድ(2021-2030) እና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎቹ ሳይንስ፣ ፈጠራ እና ቴክኖሎጂ የዘላቂ ልማት ወሳኝ አንቀሳቃሾች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን እድገት እና ልማት የሚያፋጥኑ የምርምር ስራዎችን የመጠቀም አቅም ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በውይይቱ ሁለቱ ወገኖች ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ አዳዲስ መፍትሄዎችን፣ ውጤቶችን ለማምጣት የትብብር ቁልፍ ጉዳዮችን በመለየት በቀጣይ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ለማዘጋጀት እና ወደ ስራ ለመግባት መስማማታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም