የትራፊክ አደጋ መረጃን በመሰብሰብ በማደራጀት ለፖሊሲ አውጪዎችና ተመራማሪዎች ጥራት ያለው የትራፊክ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው - አገልግሎቱ - ኢዜአ አማርኛ
የትራፊክ አደጋ መረጃን በመሰብሰብ በማደራጀት ለፖሊሲ አውጪዎችና ተመራማሪዎች ጥራት ያለው የትራፊክ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው - አገልግሎቱ
ሰመራ፤ መጋቢት 11/2017(ኢዜአ)፡- የትራፊክ አደጋ መረጃን በመሰብሰብና በማደራጀት ለፖሊሲ አውጪዎችና ተመራማሪዎች ጥራት ያለው የትራፊክ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የመንገድ ትራፊክ አደጋ መረጃ አያያዝ ስርዓት ማዘመን ላይ በአፋር ክልል ለሚገኙ የትራፊክ ፖሊስ አባላት ስልጠና ተሰጥቷል።
የአገልግሎቱ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት የህግ ትግበራ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዮናስ በለጠ የትራፊክ አደጋ መረጃን መሰብሰብና ማደራጀት ለፖሊሲ አውጪዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲዎች ምቹ ለማድረግ አገልግሎቱ እየሰራ ነው ብለዋል።
የመረጃ ስርዓቱ የትራፊክ ፖሊሶች አደጋው በደረሰበት ቦታ ላይ ሆነው አዲስ የበለጸገውን መተግበሪያ በመጠቀም መረጃዎችን በፍጥነትና በጥራት ተደራሽ በማድረግ የትራፊከ አደጋን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ለማዋል እንደሚረዳም ተናግረዋል።
አገልግሎቱ የመንገድ ትራፊክ አደጋዎችን ዳታ አያያዝ በቴክኖሎጂ ለማገዝ የሚያስችል ሶፍትዌር በማበልፀግ ስራ ላይ ማዋሉንም ገልፀዋል።
የትራፊክ መረጃን በተገቢው ጥራትና ፍጥነት በመሰብሰብ አደጋን ለመቀነስ ለሚወጡ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መጠቀም እንደሚያስችልም አብራርተዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የትራፊክ አደጋ መረጃን በተገቢው ሪፖርት ማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ ማግኘታቸውን የተናገሩት በሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር የሎጊያ ክፍለ ከተማ ትራፊክ ክፍል ኃላፊ ዋና ሳጅን አሊ ኢብራሂም ናቸው።
ስልጠናው የትራፊክ አደጋ መረጃን በጥራት ለመሠብሰብና ለሚመለከተው አካል ለማድረስ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆናቸውም ተናግረዋል።
የአውሲ ረሡ ዞን የትራፊክ ዘርፍ ኃላፊ ዋና ሳጅን ሐሰን መሐመድ በበኩላቸው ስልጠናው ከዚህ በፊት የነበረውን የትራፊክ አደጋ ፍሰትና ሪፖርት አደራረግን እና መዝገብ አያያዝ ላይ የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ስልጠናው ወጥነት ባለው መልኩ የትራፊክ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ያሉት ደግሞ የአዋሸ ሰባት ከተማ የትራፊክ ክፍል ኃላፊ ዋና ሳጅን መሐመድ አህመድ ናቸው።
የመረጃ ስርዓቱ የትራፊክ አደጋ በደረሰበት ቦታ ጥራት ያለው መረጃ ለማግኘትና መዝገቦችን በማደራጀት ለሚመለከተው አካል ለማሳወቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የሚሌ ከተማ የትራፊክ ዘርፍ ኃላፊ ዋና ሳጅን ሃሰና አብዱ በበኩላቸው ሥልጠናው የትራፊክ አደጋ መረጃዎችን በፍጥነትና በቴክኖሎጂ በታገዘ እና ወረቀት አልባ በሆነ መንገድ በቅልጥፍና ለማስተላለፍ ያግዛል ነው ያሉት።
በተለይም ስርዓቱ ኔትዎርክ ተደራሽ ባልሆነባቸው ስፍራዎች ሁሉ መስራቱ ስራችንን ያቃልላል ሲሉም ገልጸዋል።