ቀጥታ፡

ያልተነኩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለአሜሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2017(ኢዜአ)፦ያልተነኩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለአሜሪካ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተገለጸ።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብናልፍ አንዱአለም ከኢትዮ-አሜሪካ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና ከምክር ቤቱ የቦርድ አባላት ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ባለው የቢዝነስ ትስስር ዙሪያ መምከራቸው ተገልጿል።

የንግድ ምክር ቤቱ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ትስስር እንዲጠናከር ለሚያበረክተው አስተዋጽኦ ያመሰገኑት አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ካለው ሰፊ ገበያና ሀብት አንጻር የበለጠ መስራት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ፖሊሲ በንግድና ኢንቨስትመንት ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑን በመጥቀስ፤ በሀገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን የወጪ ምርቶችና ያልተነኩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለአሜሪካ የንግድና ኢንቨስትመንት ኩባንያዎች በይበልጥ ማስተዋወቅ እንደሚገባም አምባሳደሩ አስገንዝበዋል።

ምክር ቤቱ በሚሳተፍባቸው የንግድና ኢንቨስትመንት መድረኮች ላይ ለአሜሪካ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በይበልጥ እንዲያስተዋውቅ ጥሪ ማቅረባቸውን በአሜሪካን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የምክር ቤቱ አመራር በበኩላቸው በአሜሪካ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ የኢትዮጵያ ምርቶችን በማስተዋወቅ ተጨማሪ የውጭ ገበያ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በዚህም ረገድም መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ያላቸውን ሙሉ እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም