ቀጥታ፡

ህዳሴ ግድብ የኢኮኖሚ ጫናን በራስ አቅም የመቀልበስና ተባብሮ የመስራት ድልን አጉልቶ የሚያሳይ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2017(ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢኮኖሚ ጫናን በራስ አቅም የመቀልበስና ተባብሮ የመስራት ድልን አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በታለመለት መልኩ በራስ አቅም ተገንብቶ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አንስተዋል።

ህዳሴ ግድብ በመሞላቱ ምክንያት አሰዋን ግድብ ላይ የጎደለ ውሃ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም መንግስት ቃል የገባው በተግባር ተሳክቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሁለቱንም የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ስታካሂድ ለነበረው ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ምላሽ የሚሰጥ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ኩራት መሆን የመቻል ተምሳሌትና ስህተትን የማረም ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል።

እንዲሁም የኢኮኖሚ ጫናን በራስ አቅም የመቀልበስና ተባብሮ የመስራት ድልን አጉልቶ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

መንግስት ይህንን ታሳቢ በማድረግ ግድቡ በታለመው ልክ በጥራት ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ህዝቡን በማስተባበር ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።

በመሆኑም በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ እንደሚመረቅ ገልጸው፤ ይህም የኢትዮጵያ አኩሪ ታሪክ ሆኖ ይመዘገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም