ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመቀሌ ቅርንጫፍ በተያዘው ወር መጀመሪያ ሳምንት ስራ ጀምሯል

መቀሌ፤መጋቢት 10 /2017(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመቐለ ቅርንጫፍ በመጋቢት ወር መጀመሪያ ሳምንት ስራ መጀመሩን አስታወቀ።
 
የቅርንጫፉ ስራ አስኪያጅ አቶ ክብሮም ፀጋይ ለኢዜአ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመቐለ ቅርንጫፍ በተያዘው መጋቢት ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ ስራ ጀምሯል። 
 
በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ስራ የተጀመረው የሰሊጥ ምርት ከአርሶ አደሮች በመረከብ መሆኑንም ገልፀዋል። 
 
በክልሉ የሰሊጥ፣ የማሾና የዕጣን ምርቶች ወደ ገበያ ስርዓቱ የገቡ መሆኑን ጠቅሰው አገልግሎት በመጀመሩ አርሶ አደሩ ያመረተው ምርት በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት እንዲያልፍ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል። 



የቅርንጫፉ ዋና አላማም በክልሉ የሚገኙ አርሶ አደሮችና ላኪዎች ዘመናዊና ቀልጣፋ የገበያ ስርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። 
 
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለመቀሌ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ ማሽኖችና ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ እያከናወነ  መሆኑንም አክለው ገልጸዋል። 
 
የመቀሌ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት በአገሪቱ ከተከፈቱ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች 26ኛው መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም