የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትሃድ አየር መንገድ በትብብር ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትሃድ አየር መንገድ በትብብር ለመስራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢትሃድ አየር መንገድ የአየር ትራንስፖርት ትስስርን ለማጠናከር የሚያስችል ስትራቴጂክ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ ለደንበኞች የተቀላጠፈ የበረራ አማራጭ ለማቅረብ በሁለቱ አየር መንገዶች “የኮድ ሼር” አገልግሎት እና በአዲስ አበባ እና አቡዳቢ መካከል የበረራ አገልግሎት መጀመርን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
በስምምነት መርሐግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ፣ የኢትሃድ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ መሀመድ አሊ አል ሾራፋ እንዲሁም የሁለቱም አየር መንገዶች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየርመንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ከኢትሃድ አየር መንገድ ስራ አስፈጻሚ አንቶናልዶ ኔቬስ ጋር ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ስምምነቱ የሀገራቱን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።
ስምምነቱ እውን እንዲሆን ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትሃድ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ መሀመድ አሊ አል ሾራፋ እንደገለጹት ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ትስስር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው ስምምነቱ ታሪካዊ መሆኑን ጠቅሰው፤ አየር መንገዱ አፍሪካን ከተቀረው አለም ጋር እያገናኘ ያለ መሪ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
ስምምነቱ ግንኙነትን ለማስፋት እንዲሁም ተቋማቱ እድገታቸውን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትሃድ አየር መንገድ ስራ አስፈጻሚ አንቶናልዶ ኔቬስ በስምምነቱ መሰረት አየር መንገዶቹ በጋራ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
አላማቸውንም ለማሳካት በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸው ይህን እውን ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።