ለጨቅላ ህጻናት ህክምና የሚውል ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለጨቅላ ህጻናት ህክምና የሚውል ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 10/2017(ኢዜአ):-ለጨቅላ ህጻናት ህክምና የሚውልና ግምቱ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር የሆነ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
ድጋፉ በጤና ሚኒስቴር ባለቤትነትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አጋርነትለሚከናወነው የህጻናትን ህይወት ለመታደግ የሚተገበረው ፕሮግራም(The Saving Little Lives (SLL) በኔስት 360 አለም አቀፍ ጥምረት አማካኝነት የተደረገ ነው ተብሏል፡፡
የህጻናትን ህይወት ለመታደግ የሚተገበረው ፕሮግራም በጌትስ ፋውንዴሽን ፣በኢምላ ፊላንትሮፒና በቻይልድ ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን እገዛ የሚደረግለት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕሮግራሙ ዳይሬክተር አብይ ሰፋ ድጋፉን ለጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ አስረክበዋል።
ድጋፉ የጨቅላ ህፃናት ዲጂታል ሚዛንና ማሞቂያ ማሽንን ጨምሮ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው።
በዚሁ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።
ህፃናት ከመወለጃ ጊዜያቸው ቀድመው ሲወለዱ በአብዛኛው የክብደት መጠናቸው ከ 2 ነጥብ 5 ኪሎ በታች እንደሚሆን ጠቅሰው፥ ይህም ጨቅላ ህጻናትን ለሞት ከሚዳርጉ ምክንያቶች ዋነኛው መሆኑን አስታውቀዋል።
የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የህክምና ክፍሎችን በአስፈላጊ ቁሳቁሶች ማሟላት አስፈላጊ በመሆኑ ድጋፉ ለኦሮሚያ፤አማራ፤ትግራይ ፤ሲዳማና አፋር ክልሎች የሚሰራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፕሮግራሙ ዳሬክተር አቶ አብይ ሰፋ በበኩላቸው፥በአገር አቀፍ ደረጃ የእናቶችንና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚሰሩ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የተደረገው ድጋፍ የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስና የህጻናቱን ጤና ለመጠበቅ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።
የእናቶችና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ በሚሰሩ ስራዎች ላይ በቀጣይ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋለ።
በተያያዘም በአለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የአፍና የጥርስ ጤና አጠባበቅ ቀንን የአፍ ጤና ምርመራና የአፍ ጤና አጠባበቅ ላይ ግንዛቤ በመስጠት ተከብሮ ውሏል፡፡