ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልእኮ የገነባችውን ዓለም አቀፍ ክብርና ዝና ጠብቆ ለማስቀጠል ተዘጋጅተናል-የሰራዊቱ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልእኮ የገነባችውን ዓለም አቀፍ ክብርና ዝና ጠብቆ ለማስቀጠል ተዘጋጅተናል-የሰራዊቱ አባላት
ድሬዳዋ፤የካቲት 10/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልእኮ የገነባችውን ዓለም አቀፍ ክብርና ዝና ጠብቆ ለማስቀጠል ተዘጋጅተናል ሲሉ ለሰላም ማስከበር የሰለጠኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ገለጹ።
ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልእኮ ከአህጉርም ባለፈ በዓለም የገዘፈ ክብር፣ስምና ዝና ያላት ሀገር መሆኗ ይታወቃል።
በዚህ ረገድ የሰራዊቱ ታማኝነት፣የላቀ የመፈፀም አቅምና ብቃት እንዲሁም ጀግንነቱ የተመሰከረለት ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልእኮ የገነባችውን ዓለም አቀፍ ክብርና ዝና ጠብቆ ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ለሰላም ማስከበር የሰለጠኑ የሰራዊቱ አባላት ተናግረዋል።
በሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የሰላም ማስከበር ስልጠና አጠናቀው ከተመረቁት የሰራዊቱ አባላት መካከል ምክትል አስር አለቃ ስዩም ተስፋዬ፥በሰላም ማስከበር ተልእኮ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የገዘፈ ስም ያላት መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሰራዊት በተለያዩ የዓለም አገራት በመጓዝ በሰላም ማስከበር የላቀና የተሳካ ተግባር በመፈፀም በአርአያነት የሚነሳ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የካበተና የላቀ የሰላም ማስከበር ተልእኮ ዓለም አቀፍ ክብርና ዝና ጠብቆ ለማስቀጠል ተዘጋጅተናል ሲሉ አረጋግጠዋል።
ከሰራዊቱ አባላት መካከል ምክትል አስር አለቃ አስቴር ደሬ፥የኢትዮጵያን የሰላም ማስከበር ሚና፤ የሠራዊቱን ጀግንነትና ህዝባዊ ወገንተኝነት ጠብቆ ለማስቀጠል ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነን ብለዋል።
የሀገሬ ጉዳይ የማንነቴና የክብሬ ጉዳይ በመሆኑ በቁርጠኝነት ተልእኮየን ለመፈፀም ዝግጁ ነኝ" ሲሉም ተናግረዋል።
ምክትል አስር አለቃ ይስሃቅ ኢሚቶ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በሰላም ማስከበር ታሪክ ያለውን ዓለም አቀፍ ተቀባይነትና አኩሪ ታሪክ በከፍታው ልክ ጠብቀን ለማስቀጠል ዝግጁ ነን ብለዋል።
ሌላኛዋ የሰላም አስከባሪ ወታደር አምሳለ ሶሬሳ፥የሀገራችንን ስም ይበልጥ በማስጠራት በታማኝነትና በታታሪነት የሰላም ማስከበር ሚናችንን አጠናክረን ለመቀጠል ተዘጋጅተናል በማለት ተናግረዋል።