ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሹ ገለጹ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 10/2017(ኢዜአ):-ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ከሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ ቢን አብዱልከሪም ኤልኬሬጂ ( ኢ/ር) በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ውይይቱ በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን በኢኮኖሚ ዘርፍ ያለውን የአገራቱን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ተነስቷል።

ሚኒስትሩ በቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያም በተለይ ሱዳንን በተመለከተ ከምክትል ሚኒስትሩ ጋር መክረዋል።

ኢትዮጵያ ገለልተኛ አቋም የምታራምድ እና እንደ ጎረቤት እና ወዳጅ ሀገር ሱዳን ያጋጠማት ችግር እንዲፈታ ወጥ በሆነ መንገድ መፍትሔ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ ገልጸዋል።

የሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ ቢን አብዱልከሪም ኤልኬሬጂ (ኢ/ር) አገራቸው የሱዳን ቀውስ መቋጫ እንዲያገኝ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደምትሰራ ገልጸዋል።

በተያያዘም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከሳዑዲው አቻቸው ጋር ውይይት አድርገዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል የኢኮኖሚ ትስስር በሚጠናከርበት መንገድ፣ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች እና ሌሎች የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ፥ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል በመፍጠሩ የሳዑዲ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ጠይቀዋል።

የሳዑዲው አቻቸው ዋሊድ (ኢ/ር) በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በግብርና ዘርፍ፣በማዕድን ፣ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ ናት ብለዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ አንድ የደኀንነት ስጋት አድርጎ እንደሚወስደው ጠቅሰዋል።

አደጋውን ለመከላከል ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ጠንካራ ትብብር ማድረግ እንደሚፈልግ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም