ቀጥታ፡

ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አርባ ምንጭ፤መጋቢት 10/2017 (ኢዜአ)፦ባለፉት ስምንት ወራት ወደ ውጭ ከተላከ የቡና ምርት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል።

በዚህን ጊዜ የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታጋይ ኑሩ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ከቡናው ዘርፍ የተሻለ ገቢ ለማግኘት በተቀናጀ መንገድ ሲሰራ ቆይቷል።

በዚህም ባለፉት ስምንት ወራት ከ250 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ወደውጭ በመላክ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

ገቢው ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 140 በመቶ ጭማሪ እንዳለውም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የቡና ምርትና ምርታማነት ማደግ እንዲሁም የዓለም የቡና ዋጋ መጨመር ለገቢው ማደግ ምክንያት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ታጋይ ገለጻ በሀገሪቱ ከ2 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ ማሣ ላይ ቡና እየለማ ሲሆን በልማቱም ከ25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እየተሳተፉ ነው።

በበጀት ዓመቱ ከቡና ምርት ሽያጭ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም