ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙሃን የጋራ ትርክትን በመገንባት ሒደት ኃላፊነታቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤መጋቢት 10/2017(ኢዜአ):-መገናኛ ብዙሃን ለዘላቂ ሰላምና ለጋራ ትርክት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ይበልጥ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የሰላም ጋዜጠኝነት ጽንሰ ሃሳብን በሚመለከት በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በኩል ክፍተት ይስተዋላል።

የሰላም ጋዜጠኝነት መርህ የሰላም እጦት አዝማሚያን በመረዳት ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ መረጃዎችን ቀድሞ ማክሰምና የሰላም አስፈላጊነት ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም የዜጎችን ደህንነት፣የአገርን ሰላም ብሎም ብሔራዊ ጥቅም ማስቀደምና ማክበር መሆኑንም አብራርተዋል።

ለዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ ቀደም ሲል የነበሩ የሰላምና የአብሮነት እሴቶችን አጉልቶ ማሳየትና ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ለግጭት ዘገባ የሚሰጠውን ትኩረት በመቀልበስ ሰላምን የሚያጎለብቱ ስራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባም ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በኩል የሰላም ጋዜጠኝነት ጽንሰ ሃሳብ ምንነትና አተገባበር ላይ ውስንነቶች እንዳሉ የሚያመላክቱ ስራዎች ሲሰሩ ይስተዋላል ብለዋል።

በመሆኑም ጽንሰ ሃሳቡን በአግባቡ መረዳትና በኃላፊነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ይህም አንደ አገር የጋራ ትርክትን ለመገንባት እየተከናወኑ ባሉ ተግባራቶች ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አሻራቸውን በማኖር ለሰላም ግንባታ አስተዋጽኦዋቸውን ማበርከት ይገባቸዋል ብለዋል።

ለዚህም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የክትትልና ቁጥጥር ስረዓቱን የሚያጠናክሩ አሰራሮችን እየዘረጋ ስለመሆኑ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አንተነህ ፀጋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ መገናኛ ብዙሃን የአገርን ገጽታ በማስተዋወቅና በትውልድ ግንባታ ላይ አይነተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።

በተለይም የአገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር፣በሰላም ግንባታ ተግባራት ላይ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ለሰላም መደፍረስ ምክንያት የሚሆኑ መረጃዎች ሲያሰራጩ ይስተዋላል ብለዋል።

ይህም በአገረ ግንባታ ሒደት ላይ አሉታዊ ተጽእኖን ከማሳደር ባሻገር በዜጎች አብሮነት ላይ ጫና ሊያስከትል እንደሚችል ጠቅሰው፥አሰባሳቢ እሴቶችን ማጉላት፣ለትውልድ ማስተላለፍና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በየትኛውም መስክ የተሰማሩ መገናኛ ብዙሃን በሰላም፣ በአገር ብሔራዊ ጥቅምና መሰል ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አረዳድ በማሳደግ ለህዝቦች አብሮነት መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

በዚህም መገናኛ ብዙሃን የጋራ ትርክትን በማስረጽ ረገድ ያላቸውን አቅም አሟጠው መጠቀም እንዳለባቸው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም