ባንኩ በረመዳን ወር ያደረገልን ድጋፍ የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴትን የሚያጠናክር ነው--የሠመራ ሎጊያ እና የዱብቲ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ በረመዳን ወር ያደረገልን ድጋፍ የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴትን የሚያጠናክር ነው--የሠመራ ሎጊያ እና የዱብቲ ነዋሪዎች
ሰመራ፤ መጋቢት 10/2017 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በረመዳን ወር ያደረገላቸው የማዕድ ማጋራት የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴትን የሚያጠናክር ነው ሲሉ ድጋፍ የተደረገላቸው የሠመራ ሎጊያ እና የዱብቲ ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠመራ ቅርንጫፍ ከኢስት አፍሪካ ፋርማሲቲካልስ እና ኢማን ኢስላሚክ አሶሴሽን ጋር በመተባበር በሰመራ ሎጊያና የዱብቲ ከተሞች አነስተኛ ገቢ ላላቸው 350 ወገኖች ጾሙን ምክንያት በማድረግ ዛሬ ማዕድ አጋርቷል።
በማዕድ ማጋራት መርሀግብሩ ላይ ተገኝተው የምግብ ድጋፉን ያስረከቡት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የአፋር ክልል ወጣቶች ባህልና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሐሚድ ዱላ እንደገለጹት፣ የረመዳን ወርን ምክንያት በማድረግ በባንኩና በተባባሪ አካላቱ የተደረገው ድጋፍ የአብሮነትና የመተጋገዝ ባህል ማሳያ ነው።
ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ማገዝ፣ መጎብኘትና ማስታወስ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል አንዳለበትም ነው ኀላፊው ያብራሩት።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰመራ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሰሚር አማረ በበኩላቸው ባንኩ ላለፉት ዓመታት ድጋፍ የሚያሻቸውን ወገኖችን በተለያየ መንገድ ሲያግዝ መቆየቱን ተናግረዋል።
በዛሬው እለትም ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በከተሞቹ ለሚገኙ ለ350 ድጋፍ የሚሹ ወገኖች የምግብ ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል።
በዚህም ዘይት፣ ፖስታ፣ ሩዝና ዱቄት መለገሱን ተናግረዋል።
በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት አቶ ሰሚር፣ የኢፍጣርና የኢድ ልዩ ፕሮግራም ለማዘጋጀትም መታቀዱን ጠቁመዋል።
በእለቱ የተገኙት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲቢኢ ኑር ዳይሬክተር አቶ አንዋር አብደላ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የረመዳን ወርን ምክንያት በማድረግ አነስተኛ ገቢ ላለቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፋር ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የሃጂና ኡምራ ዘርፍ ዳይሬክተር ሃጂ መሐመድ ሷሊህ "ባንኩ የረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ያደረገው ድጋፍ ለሌሎች በአርአያነት የሚታይ ነው" ብለዋል።
በዛሬው ዕለት ድጋፍ ከተደረገላቸው ወገኖች መካከል አቶ መሐመድ አህመድ ለተደረገላቸው የምግብ ድጋፍ አመስግነዋል።