አፊኒ ሶንጎ

በሀብታሙ መኮንን (ከሀዋሳ ኢዜአ)

ኢትዮጵያ ሠላሟ ፀንቶ፣ ህዝቦቿም ወንድማማችነትና አብሮነታቸው ደምቆ እንድትቀጥል የሚያስችሏት የበርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ናት።

ለጠብ የሚጋበዙትን በእርጥብ ቄጤማ አቀዝቅዘው የሚያበርዱ፣ በቂም ቁርሾ ተነሳስተው በነፍስ የሚፈላለጉትን በባህል እሴት አስረው በፍቅር የሚያዋድዱ የበርካታ ማንነቶች ባለቤት ናት - ሀገራች ኢትዮጵያ።

የሲዳማ “አፊኒ”፣ የራያ “ዘወልድ”፣ የኦሮሞ “ጃርሱማ”፣ የጋሞ “ዱቡሻ”፣ የጌዴኦ “ጎንዶሮ”፣ የጉራጌ “የጆካ”፣ የካፋ “ቃብትኖ” እና በየአካባቢው ያሉ ሌሎች ሀገር በቀል የእርቅና የሠላም እሴቶች ሰላምን በማውረድ ለዘመናት ተከባብረው የኖሩ ህዝቦችን የፈጠሩ የጋራ ማንነት ውጤቶች ናቸው።

“አፊኒ” የተሰኘው ባህላዊ የዳኝነት ሥርዐት የሲዳማ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ የተጣላን ሲያስታርቅበት፣ "በደሌን ስሙልኝ" ብሎ ለቀረበ አቤቱታ አቅራቢ ደግሞ ጉዳዩን መርምሮና “ሀላሌ”ን ገልጦ በዳይ እንዲክስ፤ ተበዳይ ደግሞ እንዲካስ የሚያደርግ ነው። ችግሩን በዕርቀ ሠላም ቋጭቶ፣ ተመራርቆና “ማጋኖ”ን አመስግኖ የሚኖርበት ቱባ እሴት ነው ማለትም ይቻላል፡፡

በሲዳማዎች ዘንድ እንዲህ ይነገራል “ጥንት ማጋኖና የሰው ልጆች አብረው ይኖሩ ነበር። 

ከጊዜያት በኋላም ማጋኖ የሰው ልጆችን ምድር ላይ ትቶ ወደ ሰማይ የሚሄድበት ጊዜ ደረሰ። 

በዚህን ጊዜ ሽማግሌዎች ማጋኖን "እኛን ለማን ትተኸን ትሄዳለህ" ሲሉ ጠየቁት። 

ማጋኖም "ለእናንተ ሀላሌን እተውላችኋለሁ" ብሎ ሀላሌን በሽማግሌዎች እጅ አኑሮ ሄደ ይባላል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሲዳማ ሰማይ ስር ሁሌም “ሀላሌ” ባለበት “ማጋኖ” በመንፈሱ አለ ተብሎ ይታሰባል።

“ሀላሌ” በሲዳማዎችና በ“ማጋኖ” መካከል ያለ የቃልኪዳን ውል ነው።

በሲዳማዎች ዘንድ “ሀላሌ” የሁሉ ንጉስና ፈጣሪ ከሆነው “ማጋኖ” የተበረከተ እልፎች የሚገዙለት ረቂቅ ንጉስ ተደርጎም ይወሰዳል። 

መናገሻ አደባባዩ ደግሞ “አፊኒ ሶንጎ” ይባላል።


 

አንድ የሲዳማ ተወላጅ “ማጋኑ ሀላሌቲ” ካለ ትርጉሙ የፈጣሪ ዕውነት እንደማለት ሲሆን አንድም ትልቁን መሀላ እየማለ፤ አንድም ደግሞ የእውነት ምንጭ ፈጣሪ መሆኑን እየገለጸ ነው፡፡

በዘመነኛው ዓለም የዕውነት ትርጓሜው ብዙ፤ ፍልስፍናውም ውስብስብ ነው። ይህ ዓለም አንዳንዴም "ዕውነት አንፃራዊ ነው" የሚል ፍልስፍናዊ ድምዳሜ ይሰጣል። ሰዎች ያመኑበት ሀሳብ ለእነርሱ እውነት ነው፡፡

በአንፃሩ ይህ ሀሳብ በሌሎች ዘንድ ላይታመንበትና እውነት ላይሆን ይችላል። በአራቱም ጫፍ ላሉ ሲዳማዎች ግን ዕውነት ማለት “ሀላሌ” ነው፡፡ 

እንዳይጨመርበት ምሉዕ፤ እንዳይቀነስበት ልክ የሆነ፤ ረቂቅ ሆኖ የሚጨበጥ አንድ ቃል ሆኖ ሺህ ቃላትን የሚረታ የፈጣሪ እውነት።

“ሀላሌ” ከነ ሙሉ ክብሩ የሚነግስበት የ“አፊኒ” ሥርዐት የሚካሄድበት የሸንጎ አደባባይ ደግሞ “አፊኒ ሶንጎ” ይባላል።

“አፊኒ” የሲዳማ ህዝብ ያዳበረው የሠላምና የአብሮነት እሴት የሚታይበት ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ነው።

እንደ ሀገር እየተተገበሩ ካሉ የሪፎርም ሥራዎች መካከል ባህላዊ የዕርቅና የዳኝነት ሥርዐቶችን ማጎልበትና ተሞክሮዎችን በማስፋት ህብረተሰቡ በመደበኛነት እንዲገለገልባቸው ማድረግ የሚጠቀስ ነው።

የ“አፊኒ” ባህላዊ የዳኝነት ሥርአትን ጠብቆ ያቆየውና ባለቤት የሆነው የሲዳማ ህዝብ በስፋትና በላቀ ደረጃ መጠቀም እንዲችል የሲዳማ ክልል መንግስት ሥርአቱ በሕግ ማዕቀፍ እንዲደገፍ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ተጨባጭ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት የ“አፊኒ ሶንጎ” ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 42/2016ን በማፅደቅ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዐቱ ሕጋዊ ሰውነት ኖሮት ህዝቡ መገልገል እንዲችል መሰረት ጥሏል፡፡ 

ይህን አዋጅ መሰረት በማድረግ የሚመለከታቸው የክልል አካላት ከፌዴራል አካላት ጋር በመሆን የቅድመ ዝግጅትና የአደረጃጀት ሥራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡

በዚህም መሠረት የ“የአፊኒ ሶንጎ” ማቋቋሚያ እና እውቅና መስጫ መርሀ ግብር ባለፈው የካቲት ወር በተለያዩ ወረዳዎች የተካሄደ ሲሆን ባህላዊ የዳኝነት ሥርዐቱ በሁሉም ወረዳዎችና ቀበሌዎች በመደበኛነት አገልግሎት እንዲሰጥም ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሀግብርም ተካሂዷል ፡፡


 

የፍትሕ ሚኒስቴር ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል ተግባራዊ እያደረገ በቆየው የሦስት ዓመት ሀገራዊ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ውስጥ በህብረተሰቡ ውስጥ ላሉ ባህላዊ የፍትህ ሥርዐቶችን ትኩረት ሰጥቷል። እነዚህን ማጠናከርና ህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ እንዲገለገልባቸው ማድረግ ቀዳሚ ትኩረቱ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን ይናገራሉ፡፡

በዚህም “አፊኒ”ን ጨምሮ በየአካባቢው ያሉ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዐቶች በህብረተሰቡ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት የጎላ በመሆኑ በልፅገውና ዳብረው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ብሎም የፍትሕ ሥርአቱ ያሉበትን ክፍቶች መሙላት እንዲችሉ ሚኒስቴሩ ሙያዊና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።

ይህ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዐት ከዘመናዊው የፍትሕ ሥርዐት የሚለይበት የራሱ ባህሪያት ያሉት ሲሆን ሲዳማዎች ታላቅ ከበሬታን የሚሰጡትና የፍቅር ሸማቸውን የሚቋጩበት ድንቅ መገለጫቸው ነው፡፡

ዘመነኛው የፍርድ ችሎት ምስክሮችን ቆጥሮ ማስረጃዎችን አጣርቶ ፍርድ ይሰጣል፣ በዚህ የፍርድ ሂደት ውስጥ በምስክርና በማስረጃ የረታ ይፈረድለታል የተረታ ደግሞ ይፈረድበታል።

በክርክር መሀል አሸናፊና ተሸናፊን የሚለየው ሕጋዊ እውነት ነው፤ የሚቀርበው መረጃና ማስረጃ ነው።

በርግጥ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች የሚሰየሙ ችሎቶች ምስክሮችን እንደየሃይማኖታዊ አስተምህሮታቸው መሀላ እንዲፈፅሙ ማድረጋቸውን ልብ ይሏል ፡፡


 

የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትልና የባህል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳዊት ዳንጊሶ እንደሚያስረዱት በ“አፊኒ ሶንጎ” ላይ በዳኝነት የሚሰየሙት ሽማግሌዎች ወይም በሲዳማዎች አጠራር “ጪሜሳ”ዎች ናቸው። የዳኝነት ስርአቱን ሲያከናውኑ መነሻቸውም መደምደሚያቸውም  “ሀላሌ” ብቻ ነው፡፡

እነኚህ የዕድሜ ፀጋን ከብልሀት ጋር ደርበው የለበሱ ሽማግሌዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተአማኒነትና ክብር ያላቸው ሲሆኑ እውነትን መርምሮ የማውጣት ጥበብን የተካኑ ናቸው፡፡ 

“ሀላሌ”ን ለማግኘት አብዝተው ይተጋሉ፣ ለፍርድም የማይቸኩሉ በሳሎች በመሆናቸው ጉዳዩ ውስብስብ ቢሆን እንኳ እውነቱን ሳያገኙ ለፈርድ አይቸኩሉም። እውነት የዳኝነት ሥርዐቱ የህልውና መሠረት ነውና ሳይታክቱ ይመረምራሉ፤ ይተጋሉ፡፡ በዚህ መሠረት ስለሚሰሩ በሁሉም ወገን ቅቡልነት ያለው ፍትሕን ያሰፍናሉ፡፡ 

የዳኝነት ሥርዐቱ መደምደሚያ ዕርቀ ሠላም ነውና ሁለቱም ወገኖች ይታረቃሉ፤ ሽማግሌዎችም ዳግም ቅራኔ ውስጥ እንዳይገቡ መርቀዋቸው፤ “ሀላሌ”ም ከሰዎች ልቦና እንዳይርቅ “ማጋኖ”ን ተማፅነው ጉዳዩን ይቋጩታል፡፡

ኢትዮጵያ ሠላሟ እንዲጸና አብሮነትና ወንድማማችነት ደምቆ እንድትቀጥል የሲዳማ አፊኒን ጨምሮ በየአካባቢው ያሉ ሌሎች ሀገር በቀል የእርቅና የሰላም እሴቶች በእጅጉ እንደሚያስፈልጓት አሌ የማይባል ሀቅ ነው።

ሆኖም እንደ ሀገር ቀደም ባሉት ጊዜያት ለባህላዊ እሴቶችና ለሀገር በቀል እውቀቶች ትኩረት ተነፍጎ በመቆየቱ የመደብዘዝ እጣ ፈንታ ገጥሟቸው ነበር፡፡ “አፊኒ”ም ለሰላምና ለአብሮነት ባለው ፋይዳ ልክ ሳይጎለብት፣ በሚገባ ሳይተዋወቅና ህዝቡም በሚፈለግው ልክ ሳይጠቀምበት ቆይቷል፡፡

አሁን ግን መንግስት ለባህል እሴቶች በሰጠው ትኩረት ለ“አፊኒ” ዘመን የሰመረለት ይመስላል፡፡ በክልሉ ባሉ 656ት ቀበሌያት “አፊኒ ሶንጎ”ዎች ይሰየማሉ፡፡ “ሀላሌ”ም በነዚህ ሸንጎዎች ላይ ይነግሳል፡፡ ያኔ በሲዳማ ሰማይ ሥር ወትሮም የማትጠፋው የእውነት ፀሐይ ደመናዋን ገልጣ ይበልጥ ትደምቃለች፡፡

ነባር “አፊኒ ሶንጎ”ዎች ባሉባቸው ቀበሌያት ሸንጎዎቹ በላቀ ደረጃ ህዝቡ እንዲገለገልባቸው ዕውቅና የሚሰጣቸው ሲሆን በሌሉባቸው ቀበሌያት ደግሞ በአዲስ መልክ ይቋቋማሉ፡፡ 

እነዚህ ሸንጎዎች ከጋብቻ ፍቺ በስተቀር ሁሉንም ፍትሐብሔራዊ ጉዳዮችን እንዲሁም በግል አቤቱታ የሚቀርቡ የወንጀል ጉዳዮችን እንደሚመለከቱ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መብራቴ መስፍን ይገልጻሉ ፡፡

በወረዳና ከተማ አስተዳደር መዋቅሮችም የወረዳ “አፊኒ ሶንጎ” የሚቋቋም ሲሆን ይህም ከቀበሌ “አፊኒ ሶንጎ” በይግባኝ የሚመጡ ጉዳዮችን ተመልክቶ ውሳኔ ይሰጣል ፡፡

በክልል ደረጃ ደግሞ “ሞቴቴ ሶንጎ” ወይም በባህላዊ አመራርነት ውስጥ ከፍተኛውን እርከን የሚይዙት “ሞቴ”ዎች የሚመሩት ሸንጎ ይደራጃል፡፡ ይህ ሸንጎ እንደ ቁንጮነቱ የሚመለከታቸው ጉዳዮችም ከፍ ያሉ ናቸው ፡፡

ለአብነት የወሰን ግጭቶችን እንዲሁም የአለባበስ፣ የለቅሶ፣ የሠርግና የጥሎሽ ሥርዐቶአች ላይ ውሳኔ የማስተላለፍ ሥልጣን የሚኖረው ሲሆን እንደ ክልል የባህላዊ ዳኝነት ሥርዐቱን አካሄድ የሚከታተልና የማረቅ ኃላፊነት በእጁ የተጣለበት እንደሆነም ነው አቶ መብራቴ የሚያስረዱት፡፡

በዚህ ውስጥ የመደበኛ ፍርድ ቤቶች ሚና የሸንጎዎችን የመጨረሻ ውሳኔ ተፈፃሚነት መከታተልና ማስገደድ ይሆናል ፡፡

“አፊኒ”ን በዚህ ልክ ማላቅ ባህላዊ እሴትን አስጠብቆ ከማስቀጠል የተሻገረ ትሩፋት አለው፡፡ ፍትሕን ፍለጋ ከማሳው ተነጥሎ ወደ ወረዳ ማዕከላትና ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ለሚሄድ አርሶ አደር ትልቅ እፎይታም ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ከቀዬው ባለ ሸንጎ ተዳኝቶ ሠላም አውርዶ ወደቤቱ ይመለሳል፤ ልማቱንም ይቀጥላል፡፡ 

ይህም አርሶ አደሩ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመመላለስ ያጠፋ የነበረውን ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበቱን በማዳን ትኩረቱን ማሳው ላይ ብቻ እንዲያደርግ ያስችለዋል፡፡

ለመደበኛ ፍርድ ቤቶችም ቢሆን ያለባቸውን የሥራ ጫና በማቅለል ቀልጣፋና የላቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ምቹ መደላድልን ነው የሚፈጥረው ፡፡

የሲዳማ ህዝብ ጠብቆ ካቆያቸውና ተጠቃሽ ከሆኑ የ“አፊኒ ሶንጎ” ዎች መካከል ልዩ ከበሬታ የሚሰጠውና ልዕልና ያለው ሸንጎ አለ። ይህም  “አቦ ዎንሾ ” ይባላል፡፡

“አቦ ዎንሾ” በክልሉ ዎንሾ ወረዳ የሚገኝ ስፍራ ሲሆን 16 ተከታታይ ትውልዶችም የተቀባበሉት የዳኝነት ሥርዐት ይካሄድበታል፡፡ 

ሥፍራው በሰው ልብ ውስጥ ያለ የሀሰትና የክፋት ተራራ እንደ በረዶ የሚያቀልጥ መንፈሳዊ ኃይል እንዳለው ይነገራል ፡፡

በቀጣይ “አቦ ዎንሾ”ን በስፋት እንመለስበታለን!

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም