ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የሁለትዮሽ ትብብራቸው ማጠናከር ላይ ያተኮረ ውይይት አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የሁለትዮሽ ትብብራቸው ማጠናከር ላይ ያተኮረ ውይይት አደረጉ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2017(ኢዜአ):- በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ከፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር አሕመድ አሊ ሲሮሄይ(ዶ/ር) ጋር በኢስላማባድ ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው የሀገራቱን የኢኮኖሚ እና ደህንነት ትብብር እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስር ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሀሳቦች ተለዋውጠዋል።
የጋራ ፍላጎትን ማዕከል በማድረግ የአፍሪካ-ፓኪስታን ግንኙነት ማጎልበት ላይም ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደር ጀማል በከር ፓኪስታን "Look Africa and Engage Africa" በተሰኘው ፖሊሲዋ ከአፍሪካ ጋር በጋራ መከባበር እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብር ለመፍጠር እያከናወነች ያለውን ስራ አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር እንደምትሻም ተናግረዋል።
የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር አሕመድ አሊ ሲሮሄይ(ዶ/ር) ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
ፓኪስታን ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን አጋርነት አጠናክሮ ለመቀጠል እንደምትሰራ መግለጻቸውን በኢስላማባድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።