በበጀት ዓመቱ በ170 ሚሊዮን ብር በጀት የቡና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ግብአቶች ተሟልተዋል - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ በ170 ሚሊዮን ብር በጀት የቡና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ግብአቶች ተሟልተዋል - ባለስልጣኑ
አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 10/2017(ኢዜአ)፡- በበጀት ዓመቱ በ170 ሚሊዮን ብር በጀት የቡና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ግብአቶችን ማሟላቱን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታጋይ ኑሩ እንደገለጹት ባለስልጣኑ ቡና በሀገር የኢኮኖሚ እድገት ላይ ያለውን ሚና ለማሳደግ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል።
የቡና፣ ሻይ እና ቅመማቅመም ልማት ሥራዎች የሚመሩበት ፓኬጆችንና ስትራተጂዎችን በመንደፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የቡናን ልማት ለማሳደግ በበጀት ዓመቱ 170 ሚሊዮን ብር በመመደብ የቡና ምርትና ምርታማነትን መጨመር የሚያስችሉ ግብአቶች የማሟላት ሥራ መከናወኑንም ገልጸዋል።
ለዚህም የችግኝ ማፊያ ፕላስቲክ፣ ዘመናዊ የመጎንደያ ማሽን፣ ዘመናዊ የችግኝ ጉድጓድ መቆፈሪያ ማሽን፣ መቀስና ሌሎች ግብአቶችን ለአርሶ አደሩ መቅረባቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
አምራች አርሶ አደሮችም ግብአቶቹን ተጠቅመው ለተሻለ ውጤት ተግተው እንዲሰሩ ተገቢ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉን አቶ ታጋይ ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን እና የአካባቢ ስነ-ምህዳርን ታሳቢ ያደረገ የቡና ልማትን ለማስፋፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የቡና ዋጋ መጨመሩን ያነሱት ምክትል ሃላፊው፣ በበጀት ዓመቱ ከቡና ሽያጭ 2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ለስኬቱ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ መሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር) በበኩላቸው ክልሉ የቡና ምርት በስፋት የሚመረትበት መሆኑን ገልጸው ለክላስተር የቡና ልማት፣ ለቡና ግብይትና ቁጥጥር ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቡና ግብይት ላይ የሚስተዋለውን የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ለመግታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የቡና ልማት፣ አመራረትና ጥበቃ ሥራን በማዘመን ክልሉ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን አበርክቶ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ቡና ለሀገር የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ጉልህ ድርሻ እንዳለው የጠቀሱት ደግሞ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ(ዶ/ር) ናቸው።
በዞኑ ከ22 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ ቡና እንደሚመረት ጠቅሰዋል።
ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የግምገማ መድረክ የባለስልጣኑ እና ከሁሉም ክልሎች የዘርፉ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።