ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ እና ሌሎችም የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል

መጋቢት 10/2017 (ኢዜአ ):-በኢትዮጵያ እና ሌሎችም የምስራቅ አፍሪካ አገራት በቀጣዮቹ ቀናት ከመካከለኛ አስከ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚጠበቅ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የአየር ሁኔታ መረጃ አገልግሎት (ኢክፓክ) አስታወቀ።

የኢክፓክ መረጃ እንደሚያመለክተው በደቡባዊ የሩዋንዳ አካባቢዎች በቀጣዮቹ ቀናት ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል።

በታንዛኒያ በርካታ አካባቢዎች በሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ኡጋንዳ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሰሜን፣ ደቡብና በመካከለኛው የሀገሪቷ አካባቢዎች በቀጣዮቹ ስምንት ቀናት መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።

በታንዛኒያ ምስራቃዊ ክፍል፣ በኬኒያ እና ሰሜን ምስራቅ ኡጋንዳ ደግሞ መጠነኛ ዝናብ የሚኖር ሲሆን በምእራብና ደቡብ ኢትዮጵያ የተወሰኑ አካባቢዎችም ተመሳሳይ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ይጠበቃል።

የምስራቅ አፍሪካ የአየር ሁኔታ መረጃ አገልግሎት (ICPAC) በኢጋድ ስር ሆኖ የአየር ትንበያና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን የሚያከናውን ቀጣናዊ ተቋም መሆኑ ይታወቃል። 

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት፤ ባለፈው ሳምንት በሰጠው መረጃ በተለይ በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በመጠንም ሆነ በሥርጭት የተሻለ ዝናብ እንደሚኖር አመላክቷል።

ከተያዘው ወር አጋማሽ በኋላም የሰሜን ምሥራቅ፣ የምስራቅ፣ ደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመጠንም ሆነ በስርጭት የተጠናከረ ዝናብ እንደሚያገኙ ጠቁሟል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም