ቀጥታ፡

ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ስራ እመርታዊ ለውጥ እየተመዘገበበት ነው - አህመዲን አህመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2017(ኢዜአ):- በአማራ ክልል ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ስራ እመርታዊ ለውጥ እየተመዘገበበት መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን አህመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የቢሮው የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የስምንት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ያተኮረ ምክክር በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በውይይት መድረኩ ላይ የቢሮው ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልሉ ምክር ቤት የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና የክላስተሩ የቢሮ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን አህመድ(ዶ/ር) እንደገለጹት ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እየተተገበረ ያለው የጥምረት ዕቅድ እመርታዊ ለውጥ እየተመዘገበበት ይገኛል።

በሰው ኃይል ግንባታ፣ የአሰራር ማዕቀፎችን ማዘጋጀት፣ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ ግብዓቶችን ማሟላት እና ምቹ የስራ ከባቢን በመፍጠር ረገድ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን አመልክተዋል።

በከተማ ልማት ክላስተሩ በስምንት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም በሁሉም ዘርፍ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት።


 

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ወንዶሰን ልሳነወርቅ ከተማ አስተዳደሩ ለሰው ተኮር የልማት ስራዎች በሰጠው ትኩረት ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የኮሪደር ልማት ስራዎች እና በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች መኖሪያ ቤት መገንባት ከተከናወኑ ስራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

በከተማው ያለው ሰላም ለልማት ስራዎች መፈጣን ወሳኝ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም