ጠንካራና ተልዕኮውን በብቃት የሚወጣ የፖሊስ ተቋም መገንባት ተችሏል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
ጠንካራና ተልዕኮውን በብቃት የሚወጣ የፖሊስ ተቋም መገንባት ተችሏል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2017(ኢዜአ)፡- በለውጡ ዓመታት በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ጠንካራና ሙያዊ ተልዕኮውን በብቃት የሚወጣ የፖሊስ ተቋም በመገንባቱ በወንጀል መከላከልና ምርመራ ስኬቶች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በለውጡ ዓመታት በፖሊስ ተቋማት የተደረገውን ሪፎርምና የተገኘውን ውጤት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ፖሊስ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱንና ፖሊሳዊ ተልዕኮውን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎችን እንዲያከናውን የሚያስችል ሪፎርም ገቢራዊ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ከየትኛውም የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የዘር እሳቤ ገለልተኛ የሆነ የፖሊስ ተቋም ተገንብቷል ብለዋል።
የፖሊስ ተቋም ሙያዊ ስነምግባርን በተላበሱ አባላት፣ በቴክኖሎጂና በአደረጃጀት ጠንካራ መሆን በመቻሉ በወንጀል መከላከልና በወንጀል ምርመራ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡
ከለውጡ ማግስት ሰብዓዊ ክብርን እሴቱ ያደረገ የፖሊስ ሃይል በመገንባቱ ከለውጡ በፊት በምርመራ ሂደት ይፈጸሙ የነበሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ሌሎችም ችግሮች እንዲቀረፉ ተደርገዋል ነው ያሉት።
ማህበረሰብ አቀፍ እና ማስረጃና መረጃ መር ሞዴል በመከተል ውጤታማ የወንጀል መከላከልና ምርምራ ሥርዓት መዘርጋቱንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በቂ የፌዴራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በማሰማራት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖርና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ያለምንም ችግር እንዲካሄዱ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ ሀገራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።
አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችና ህዝባዊ በዓላት ያለምንም የጸጥታ ሥጋት ማከናወን ያስቻለ ትልቅ አቅም መገንባቱንም ነው ያብራሩት።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሊፈጸሙ የነበሩ የሽብር ተግባራትና የተደራጁ ወንጀሎችን አስቀድሞ በማክሸፍም ኢትዮጵያ ጠንካራ የፀጥታ ተቋም እንዳላት አሳይቷል ብለዋል።
የወንጀል ምርመራ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ መደረጉን የገለጹት ኮሚሽነር ጀነራሉ፤ ምርምራው ውጤት እየተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በውጭ ይደረግ የነበረው የዘረ-መል(ዲ ኤን ኤ) ምርመራ በኢትዮጵያ መጀመሩ የወንጀል ምርመራን ውጤታማ ከማድረግ ባሻገር ከፍተኛ ወጪን ማስቀረት ማስቻሉንም ገልጸዋል፡፡