ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል ዘመናዊ የመስኖ ልማት ተሞክሮን የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ ነው

ሐረር ፤መጋቢት 10/2017 (ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል ዘመናዊ የመስኖ ልማት ተሞክሮን በሰርቶ ማሳያ በማስተዋወቅ የማስፋፋት ስራ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ የአርሶ አደሮችን የመስክ ቀን በማስመልከት ከሶስት ገጠር ወረዳዎች ለተውጣጡ አርሶአደሮች በኤረር ወረዳ በበጋ  መስኖ ልማት የልምድ ልውውጥ ተካሂዷል።


 

በክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ  የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ረድዋን ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በዘንድሮ የበጋ ወቅት 4ሺ500 ሄክታር መሬት  በመስኖ  እየለማ ነው።

በመስኖ እየለማ ያለውን ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ ቃሪያ፣ ፓፓያና ሌሎች  የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት  ለከተማው ማህበረሰብ በቀጥታ በማቅረብ  ገበያ እንዲረጋጋ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የከርሰ ምድር ውሃን በቴክኖሎጂ  በማውጣት የመስኖ ልማት  ስራው እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው ተሞክሮውን  በሰርቶ ማሳያ በማስተዋወቅ  እንዲስፋፋ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

 ከበልግ ወቅት  የግብርና ስራው ጎን ለጎንም የመስኖ ልማት ስራው  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

"አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በሚያለማው መስኖ ልምድ በመለዋወጥ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እያሳደገ ነው " ያሉት ደግሞ  በክልሉ የኤረር ወረዳ የግብርና ባለሙያ ወይዘሮ መሳይ ስለሺ ናቸው።


 

አርሶ አደሩ ቀደም  ሲል የዝናብ ወቅትን ጠብቆ  በዓመት አንድ ጊዜ  ያመርት የነበረውን ሂደት በመቀየር በመስኖ ልማቱ ሶስት ጊዜ በማምረት ተጠቃሚነቱን እያጎለበተ መሆኑን ተናግረዋል።

የኤረር ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ፋጡማ ዱሪ  በበኩላቸው  ከዚህ ቀደም  የዝናብ ወቅት በመጠበቅ ማሽላና ቦቆሎ ብቻ ያመርቱ እንደነበር አስታውስዋል ።

አሁን ላይ በበጋ መስኖ ቲማቲምና ሽንኩርት የመሳሰሉ አትክልቶችን በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው ዘንድሮም በዘሩት ዘር ምርቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።


 

"ባለው የቴክኖሎጂ አቅርቦትና የግብርና ባለሙያዎች ክትትል በመስኖ ልማቱ ህይወታችንን የሚያሻሽል ጥቅም እያገኘን ነው" ሲሉ ተናግረዋል። 

 "ከሞዴል አርሶአደሮች የመስኖ ልማት ተሞክሮ በመቅሰም  በአካባቢያችን ሳይታረሱ ፆም ያደሩ መሬቶችን ለማልማት እንሰራለን " ያሉት ደግሞ በክልሉ የድሬ ጠያራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ረመዳን አሊዪ ናቸው።


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም