ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያሳልጡ ወሳኝ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2017(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ግንባታ መስክ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያሳልጡ ወሳኝ እርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝ የአፍሪካ የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚ እና ልማት ሚኒስትሮች ቢሮ ተሰናባች ሊቀመንበር አንድሪው ቡቩምቤ ገለጹ።

የዚምባቡዌ የፋይናንስ፣ ኢኮኖሚ ልማት እና ኢንቨስትመንት ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ እና የአፍሪካ የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚ እና ልማት ሚኒስትሮች ቢሮ ተሰናባች ሊቀመንበር አንድሪው ቡቩምቤ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ቀጣናዊ የኃይል አቅርቦት ትስስርን የሚፈጥር ሰፋፊ እርምጃ እየወሰደች ነው ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ግንባታ መስክ እየወሰደች የምትገኘው እርምጃ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጎለብቱ አስደናቂ ስራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሌላ መልኩም የኢትዮጵያ መንግስት ገበያን ክፍት በማድረግ በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት የማክሮ ኢኮኖሚ መስክ የወሰዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎችም አመርቂ ውጤት ማምጣት የሚያስችሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ የተረጋጋና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ዕድገትን የሚያጠናክር የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት በየዓመቱ እከታተላለሁ ያሉት ተሳናባቹ ሊቀመንበር፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ዕድገት እያሳየ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ትልቅ የመልማትና የገበያ አቅም ያላት፤ ታታሪና ስራ ወዳድ ህዝብ የሚኖርባት ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በልዩ የኢኮኖሚ ዞንና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ዘርፎች የሰራቻቸው ስኬታማ ተግባራትም በጉልህ የሚታዩ ቀጣናዊ ኢኮኖሚን በከፍተኛ ደረጃ የሚያስተሳስሩ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ መስክ ሀገራዊ ዕድገትን በማሳለጥ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማፋጠን እያስመዘገበች የምትገኘው ስኬታማ ስራም ሀገራቸው ልምድ የምትወስድበት መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም