ቀጥታ፡

የጣና ዳር ንግሥቷ፣ ባለዘንባባዋ ሙሽራ፣ የቱሪዝም አስኳሏ ባህር ዳር ስራ ላይ ነች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2017(ኢዜአ)፡- የጣና ዳር ንግሥቷ፣ ባለዘንባባዋ ሙሽራ፣ የቱሪዝም አስኳሏ ባህር ዳር ስራ ላይ ነች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፍፁም የሰላም አየር፣ የዓይንና የመንፈስ ማረፊያ ውብ ሥፍራ የታደለችው ባህር ዳር ከመዝናኛ እስከ ግዙፍ የንግድ ስፍራዎቿ በእንቅስቃሴ ተሞልተዋል፤ ሀገሬው ከጧት እስከ ማታ ሥራ ላይ ነው ብለዋል፡፡


 

የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ከልጅ እስከ አዋቂ በልዩ ልዩ ስፖርቶች ደምቀዋል፤ ከዚሁ ጎን ለጎን ግዙፉ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ከተማዋን የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል የሚያደርጋት ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።

ሀገሬው በሥራ የደከመ አካሉንና አዕምሮውን ለማደስ ስፖርት ሲሠራ፣ በመዝናኛ ማዕከላት ሲዝናና፣ በዘንባባዋ ጥላ ስር አረፍ ሲል፣ በጣና ዳርቻ ሰብሰብ ብሎ ሲጫወት፣ በምሽት በእግር ሲንቀሳቀስ ማየት ልብን ሀሴት ያወርሳል ነው ያሉት።


 

ወቅቱ የዐቢይና የረመዳን አፅዋማት የሚፆሙበት ነው። የከተማዋ ምዕመን ሰርክ ወደ መስጂድና ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሲተምም ማየት መንፈሳዊ ኩራትን ይፈጥራል ብለዋል።

ውቧ ከተማ ልማቷን እያፋጠነች፣ ፍፁም የሰላም ድባብ፣ እረፍት አልባ የልማት ሥራ፣ ሞቅ ያለ የመዝናኛና የንግድ እንቅስቃሴ የሚታይባት ሆናለች ነው ያሉት።

ባየነው የሠላም ንፋስ የልማትና የሥራ ጥድፊያ እንዲሁም የቱሪዝም መነቃቃት ተደሰተናል። የተጀመሩ ስራዎችን ዓይናችንን ሳንነቅል በተገቢው ጥራት እንዲጠናቀቁ ክትትላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም