ኢትዮጵያ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በ12 አትሌቶች ትወከላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በ12 አትሌቶች ትወከላለች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 10/2017(ኢዜአ):- 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ከመጋቢት 12 እስከ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በቻይና ናንጂንግ ከተማ ይካሄዳል።
በሻምፒዮናው የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን ትናንት እኩለ ሌሊት ወደ ስፍራው አቅንቷል።
የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዩ መሀመድ ለልዑኩ ሽኝት አድርገዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አትሌቶች በድል እንደምትመለሱ እና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ እንደምታደርጉ አልጠራጠርም ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብም አሸናፊነት ስለለመደ የተሰጣችሁን አደራ ተቀብላችሁ አኩሪ ድል እንደምታስመዘግቡ ባለ ሙሉ እምነት ነኝ ብለዋል።
ሚኒስትሩ መንግስት ለአትሌቲክሱ እድገት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
በሽኝቱ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን እና የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል።
ልዑክ ቡድኑ 12 አትሌቶች፣ አሰልጣኞች፣ ቡድን መሪ፣ ቴክኒክ ቡድን መሪ፣ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ እና ፊዝዮቴራፒስት ያካተተ መሆኑን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በሴቶች ፅጌ ዱጉማ፣ ሀብታም ዓለሙ እና ንግስት ጌታቸው በ800 ሜትር ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።
ጉዳፍ ፀጋይ፣ ድርቤ ወልተጂ እና ወርቅነሽ መለሰ በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች የሚሳተፉ አትሌቶች ናቸው።
ፍሬወይኒ ኃይሉ እና ብርቄ ኃየሎም በሴቶች የ3000 ሜትር ውድድር ላይ ተሳታፊ ናቸው።
በወንዶች በሪሁ አረጋዊ፣ ቢኒያም መሐሪ እና ጌትነት ዋለ በ3000 ሜትር ወንዶች ውድድር ላይ ይወዳደራሉ።
አትሌት መለሰ ንብረት በ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር ላይ ይሳተፋል።
በ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር ላይ ስሙ ተካቶ የነበረው አትሌት ሳሙኤል ተፈራ በህመም ምክንያት ከቡድኑ መቀነሱም ተገልጿል።
በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ከ127 ሀገራት የተውጣጡ ከ570 በላይ አትሌቶች እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል።