ቀጥታ፡

ለክትባት ፕሮግራሞች ውጤታማነት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል - ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2017(ኢዜአ)፦ የክትባት ፕሮግራሞችን አፈጻጸም የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እንደሚገባ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ።

የ2017 በጀት ዓመት ሀገር አቀፍ የክትባት ፕሮግራም አፈጻጸም እና በክትባት መከላከል የሚደረግባቸው በሽታዎች ቅኝት ሪፖርት የግምገማ መድረክ ተካሂዷል።

ዶክተር ደረጀ ድጉማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የክትባት ፕሮግራሙ ከጤና ባሻገር ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው።


 

የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን በክትባት ላይ እያከናወነ ባለው ስራ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን አመልክተዋል።

ከሰባት ሚሊዮን በላይ ታዳጊ ሴቶች የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት(HPV) መሰጠቱ የስኬቱ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።

የሄፒታይተስ፣ የኩፍኝ እና የወባ ክትባቶችን ለመስጠት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ሳቢያ ክትባት ተደራሽ ያልሆኑና ክትባት ጀምረው ያቋረጡትን ተደራሽ ለማድረግ በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል ነው ያሉት።


 

በተለይም የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ላይ በትኩረት በመስራት ወረርሽኞችን መከላከል ትኩረት እንደሚያሻው ገልጸዋል።

ለክትባት ፕሮግራም አፈጻጸም ውጤታማነት ቅንጅታዊ ስራ ወሳኝ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በበሽታ መከላከል፣ ቁጥጥር እና በወረርሽኝ ምላሽ ላይ ውጤታማ ስራዎች ማከናወኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ በክትባት ፕሮግራም አፈጻጸም ላይ ያለው ቅንጅታዊ አሰራር እንዲጠናከር ጥሪ መቅረቡን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም