የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች የብቃት ማረጋገጫ ምዝገባና እውቅና ሥርዓት ተግባራዊ ሊደረግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች የብቃት ማረጋገጫ ምዝገባና እውቅና ሥርዓት ተግባራዊ ሊደረግ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2017(ኢዜአ)፡- የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች የብቃት ማረጋገጫ ምዝገባና እውቅና ሥርዓት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆችን አስመልክቶ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ የክልሎች የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ የመምህራን ኮሌጅ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በትምህርት ስርዓቱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በአጠቃላይ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት የተለያዩ ሪፎርሞች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።
የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ መምህራን ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
ለዚህም የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች ጥራትና ብቃት ያላቸው መምህራንን በማፍራት በኩል ተልዕኳቸውን በሚገባ እንዲወጡ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ በኩል የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች ድርሻ የላቀ ነው ብለዋል።
ብቁ እና ተወዳዳሪ መምህራንን በማፍራት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በቀጣይ ኮሌጆቹ ምዝገባ በማድረግ የብቃት ማረጋገጫ እውቅና ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱበት ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚደረግ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።