ሠራዊታችን በአለም አቀፍ ደረጃ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በላቀ ብቃት የመፈፀም ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል - ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊታችን በአለም አቀፍ ደረጃ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በላቀ ብቃት የመፈፀም ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል - ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ
ሁርሶ፤ መጋቢት 9/2017(ኢዜአ)፡- ሠራዊታችን በአለም አቀፍ ደረጃ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በላቀ ብቃትና ህዝባዊ ወገንተኝነት በስኬት የመፈፀም ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉ የመከላከያ የመሐንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ ተናገሩ።
የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያሰለጠናቸውን የሠራዊት አባላት ዛሬ አስመርቋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የመሐንዲስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ እንደተናገሩት፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተካሄደው ሪፎርም የሀገር መከላከያ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።
ይህም በአስተማማኝ አደረጃጀት፣ አሠራርና የዘመኑን ዕውቀትና የውጊያ ቴክኒክ የተላበሰ የሰው ኃይል እንዲኖር እና ተቋሙንም በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የተዋቀረ ቁመና እንዳላበሰው ጠቅሰዋል።
በዚህም ሠራዊታችን የሀገርን ሉአላዊነትና ህገ መንግስቱን የመጠበቅ ብቃቱን አሳድጎታል ብለዋል።
ሠራዊታችን በአለም አቀፍ ደረጃ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን በላቀ ብቃትና ህዝባዊ ወገንተኝነት በስኬት የመፈፀም ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለአለም ሰላም መረጋገጥ እያበረከተች ያለውን ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ በቀጣይም አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመቅሰም የተሻለ ስራ በመከወን ተመራጭ ሀገር እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል።
የዛሬ ተመራቂዎችና ሌሎች የሰላም አስከባሪ የሠራዊቱ አባላት በውጭ ሀገር ኢትዮጵያ የገነባችውን ታላቅ ስምና ዝና በመጠበቅ ፍፁም በሆነ ስነምግባር ተልዕኳቸውን በስኬት መወጣት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመከላከያ ሰላም ማሰከበር ማዕከል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ በበኩላቸው፤ በመከላከያ ተቋም የተጀመረው የለውጥ ሂደት ሠራዊታችን በሀገርና በውጭ ሰላም የማስከበር ተልዕኮን በላቀ ብቃት ለመፈፀም አስችሎታል ሲሉ ገልጸዋል።
የሰላም አስከባሪ የሠራዊት አባላት በመተባበርና በመቀናጀት በታላቅ ጀግንነት ስራቸውን እንዲፈፅሙም አስታውቀዋል።
ዛሬ የተመረቁት የሰላም አስከባሪ የሠራዊት አባላት በቆይታቸው የትኛውንም ተልዕኮ በላቀ ብቃትና ህዝባዊነት ማሳካት የሚያስችላቸው የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ትምህርት መቅሰማቸውን የገለጹት ደግሞ የሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ ናቸው።
የሠራዊት አባላት ሀገራችን የሰጠቻቸውን የሰላም ማስከበር ታላቅ ተልዕኮ በብቃት እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።