የደምና የዓይን ብሌን ልገሣን ለማሳደግ መገናኛ ብዙሃን የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - አገልግሎቱ - ኢዜአ አማርኛ
የደምና የዓይን ብሌን ልገሣን ለማሳደግ መገናኛ ብዙሃን የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - አገልግሎቱ
አዳማ፤ መጋቢት 9/2017(ኢዜአ)፡- የደምና የዓይን ብሌን ልገሣን ለማሳደግ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ባለሙያዎች የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ገለጸ።
አገልግሎቱ ለሚዲያ ባለሙያዎች ያዘጋጀው የደምና የአይን ብሌን ልገሣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ በወቅቱ እንዳስታወቁት አገልግሎቱ የደም አቅርቦት እንዲኖር እና ደም የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ህይወት ለመታደግ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በየቀኑ ሰፊ ቁጥር ያላቸው ደም የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች እንዳሉ ጠቅሰው ከደም ፍላጎትና አቅርቦት አንጻር እጥረት እንዳለ አስታውቀዋል።
አገልግሎቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ስምንት ወራት 342 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅዶ 80 በመቶ ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
አቅርቦቱን ለማሻሻልም 'መጋቢት የደም ልገሳ ወር' በሚል በመሰየም ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው በዚህም እንቅስቃሴ ብቻ 55 ሺህ ዩኒት ደም በሀገር ደረጃ ለመሰብሰብ ታቅዶ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
አገልግሎቱም ከኃይማኖት ተቋማትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
መድረኩ በተለይ የደምና የዓይን ብሌን ልገሳ ለማሳደግ የብዙሃን መገናኛ ተቋማትና ባለሙያዎች አጀንዳ ይዘው በመስራት ሚናቸውን ይበልጥ እንዲወጡ ለማስቻል ነው የተዘጋጀው።
አገልግሎቱ በዓይን ጠባሳ ምክኒያት የዓይን ብርሀናቸውን ላጡ 3ሺህ 500 ሰዎች የዓይን ብሌን በማንሳት ለተጠቃሚዎች መሰጠቱን አስረድተዋል።
በዚህ ዓመትም በሕይወት እያሉ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ከገቡ ሰዎች 282 የዓይን ብሌን ማንሳት መቻሉን አመልክተዋል።
እንዲሁም በዚህ አመት 446 ሰዎች የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል መግባታቸውን ጠቅሰው ይህም ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ጋዜጠኛ አሸናፊ ግዛው በሰጠው አስተያየት ማህበረሰቡ የሰብአዊ እርዳታን ባህል በማድረግ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖረው እንሰራለን ብለዋል።
በመድረኩ ላይ ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።