የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መራ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2017(ኢዜአ)፡- የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 20ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለውጭ ግንኙነትና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር ) ረቂቅ አዋጁን ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ አደጋዎችን ቀድሞ ለመተንበይ፣ መከላከልና መቋቋም የሚያስችል ሀገራዊ ተቋም ለመገንባት እየተሰራ ነው።
በዋናነትም ተፈጥሯዊ የአደጋ ክስተትን ለመመከትና የተረጂነትና የልመና አስተሳሰብን ለመሻገር ዘላቂ አቅም መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
የቅድመ አደጋ፣ የአደጋ ወቅትና የብሔራዊ አደጋ ተግባራትን ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ የፌዴራልና የክልል ተቋማትን የውስጥ አቅም ለመገንባት ሁሉን አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
አዋጁ ድንገተኛ አደጋዎች ሲከሰቱና ከአቅም በላይ ሲሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ የእወጃ ስርአት ለመዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም አዋጁ የሰብአዊ ድጋፍ፣ የዘላቂ ልማትና የሰላም ግንባታ እቅዶችን ማስተሳሰር የሚያስችል እንደሆነም አንስተዋል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የምክር ቤት አባሉ ዶክተር ብዙአየሁ ደገፋ በበኩላቸው፤ አዋጁ በጣም ጠቃሚና ጊዜውን የዋጅ ነው ብለዋል።
በተለይም በራስ አቅም ለመስራት፣ ከተረጂነት ለመላቀቅና ከድህነት ለመውጣት ሰፊ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የተናገሩት።