ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን በኢኮኖሚ ትብብራቸው ዙሪያ ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን በኢኮኖሚ ትብብራቸው ዙሪያ ተወያዩ
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 9/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብራቸውን አስመልክቶ ውይይት አድርገዋል።
ሁለተኛው የኢትዮ-ደቡብ ሱዳን ፎረም በግንቦት ወር 2017 ዓ.ም በጁባ ይካሄዳል።
በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ ከደቡብ ሱዳን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶንግ ኩል ማንያንግ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ የሀገራቱን የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
አምባሳደር ነቢል ማህዲ፥ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ያላቸውን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት መስክም የበለጠ ለማጎልበት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከግንቦት 18 እስከ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በጁባ ለሚካሄደው ሁለተኛ የኢትዮ-ደቡብ ሱዳን የቢዝነስ እና ኢንቨስትመንት ፎረም ኤምባሲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በውይይቱ ወቅት ፎረሙ በስኬት እንዲጠናቀቅ በጋራ ለመስራት ከመግባባት ላይ ተደርሷል።
የደቡብ ሱዳን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶንግ ኩል ማንያንግ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ የደቡብ ሱዳን ዜጎች የኢትዮጵያን ምርቶች አዘውትረው እንደሚጠቀሙ እና ምርቶቹን ለማህበረሰቡ በፍጥነትና በጥራት እንዲደርስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለም አመልክተዋል።
በሁለቱ ሀገሮች መካከል ህጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲጠናከር የተጀመረው የመሰረተ-ልማት ዝርጋታ ሂደት ወደ ትግበራ እንዲሸጋገር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን በጁባ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።