ቀጥታ፡

አማራጭ ወደብ ማስፋት የሕልውና ጉዳይ ነው- የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን የገቢና ወጪ ንግድ ለማሳለጥ የወደብ አማራጮችን ማስፋት የሕልውና ጉዳይ መሆኑን የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ገለፀ።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወጪና ገቢ ንግድን ጨምሮ በየዓመቱ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ ሲሆን፤ የህዝቧ የልማት ፍላጎትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።

የሀገሪቱ 95 በመቶ ወጪ እና ገቢ ንግድ በጂቡቲ ወደብ ብቻ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ከፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱና ከልማት ፍላጎት አንጻር በቂ እንዳልሆነ ይነገራል።

ለዚህም የባህር በር ማግኘትን እና አማራጭ ወደብን ማስፋትን የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ግልፅ አቋም በመያዝ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማሳካት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የባለሀብቶችና የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች ማህበራት የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ መጠን በየጊዜው እያደገ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም ከዕድገቱ አንጻር መሰረታዊ ምርቶችን በሚፈለገው ልክና በወቅቱ ለማስገባትና ወደ ውጭ ለመላክ ተግዳሮቶች እያጋጠሟቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ለመፍታትም አማራጭ ወደብ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዳንኤል ተመቸው አማራጭ ወደብ በበቂ ሁኔታ አለመኖሩ ከዕቃ ማጓጓዝ ፍጥነትና ከዋጋ አንፃር ክፍተቶች እንዲፈጠሩ ማድረጉን ነው ያነሱት።


 

ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገች እንደመሆኑ መንግሥት አማራጭ ወደቦችን ለማግኘት የጀመረው ጥረት ተገቢና ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።

ሀገሪቱ በተለያየ አቅጣጫ ወደብ ስታገኝ የወጪና ገቢ ንግዱን የበለጠ ለማሳለጥና ተወዳዳሪነትን ለማስፋት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የህልውና ጉዳይ የሆነውን አማራጭ ወደብ የማስፋት ሥራ እንዲሳካ ባለሀብቶችና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የሐዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ባለሃብቶች ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ህብረት ለማ በአንድ ወደብ ብቻ ጥገኛ መሆን የፈጠረውን ሁሉን አቀፍ ተግዳሮት አንስተዋል።


 

በዚሀም የሀገሪቱ የገቢና ወጪ ንግድ ከአንድ ወደብ ጥገኝነት ተላቆ በአማራጭ ወደቦችን ማስፋት እና ዘርፉን ማሳለጥ ይጠበቃል ነው ያሉት።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ባለፈው ቅዳሜ ለወጪና ገቢ ንግድ መሳለጥ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚና ላይ በተደረገ ውይይት በሰጡት ሀሳብ፤ ኢትዮጵያ ከፈጣን ዕድገቷና ካላት ሰፊ ህዝብ አኳያ አማራጭ ወደቦችን ማማተሯ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው ብለዋል።


 

ለዚህም መንግስት ከሁሉም ጎረቤት ሀገራት ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ በትብብር ለመስራትና ሀገራዊ ፍላጎትን ለማሳካት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም