ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ በቢሊዮን የሚቆጠር የቡና ችግኝ ከመትከል ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ጉልህ ሚና እየተወጣች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ በቢሊዮን የሚቆጠር የቡና ችግኝ ከመትከል ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ጉልህ ሚና እየተወጣች ነው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 9/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠር የቡና ችግኝ በመትከል የቡና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ጉልህ ሚና እየተወጣች መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከጣሊያን መንግሥት እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያ ቡና አምራቾች፣አቅራቢዎች እና በዘርፉ የእሴት ሰንሰለት ላይ የሚሳተፉ አካላትን ማገዝ የሚያስችል ብድር ይፋ ተደርጓል።
የጣሊያን መንግሥት ለዘርፉ የ10 ሚሊዮን ዩሮ የተራዘመ ብድር የፈቀደ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኘውን ብድር የማስተዳደር ኃላፊነትን ይወጣል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ የቡና ምርት የእሴት ሰንሰለት ከ5 ሚሊዮን በላይ አባውራና እማውራ ይሳተፉበታል።
ለኢትዮጵያ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት የቡና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በቡና ምርት የእሴት ሰንሰለት ላይ የፋይናንስ ችግር አንዱ ፈተና መሆኑን ጠቅሰው፣ የጣሊያን መንግስት ያደረገው የተራዘመ የብድር አገልግሎት ለዘርፉ ምርታማነት ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በተከናወኑ ተግባራት የሀገሪቱን የደን ሽፋን መጨመር መቻሏን ገልጸው፣ በመርሀ ግብሩ በቢሊዮን የሚቆጠር የቡና ችግኝ መተከሏንም ጠቅሰዋል።
በዚህም የቡና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ኢኮኖሚውን ከመደገፍ ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ወሳኝ ሚና እያበረከተች መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
የጣሊያን ልማት ትብብር ኤጀንሲ ዳይሬክተር ማይክል ሞራና የጣሊያን መንግስት የኢትዮጵያ የቡና ልማት የእሴት ሰንሰለት ለማገዝ ያሳየው ፍላጎት የሀገራቱ የጋራ ልማት ቁርጠኝነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ የቡና ልማት ከኢኮኖሚ ባሻገር ሀገራዊ መገለጫና መለያ መሆኑን ጠቅሰው፣ የጣሊያን መንግስት ለዘርፋ እሴት ሰንሰለት መሳለጥ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።
የዛሬው መድረክም የኢትዮጵያ እና ጣሊያን የአብሮነት መገለጫ መሆኑን ገልጸው፣ ለኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን መሰረት ለመጣል ትብብራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከአመራረት ጀምሮ እስከ ገበያ መዋዠቅ እንቅፋት መኖራቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ጥራት ያለው ቡና ማምረት የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ መሆሩንና የዘርፉን የእሴት ሰንሰለት ለማጠናከር ትብብሩ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።