የጥንቃቄ መልዕክት! ከአጭበርባሪዎች እንዴት ራሳችንን እንጠብቅ? - ኢዜአ አማርኛ
የጥንቃቄ መልዕክት! ከአጭበርባሪዎች እንዴት ራሳችንን እንጠብቅ?
አጭበርባሪዎች ኢላማ ያደረጓቸውን አካላት ለማጭበርበር የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ መንገዶች ቢኖሩም በስፋት ከተለመዱት የማጭበርበሪያ መንገዶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
👉በአጭር የጽሁፍ መልዕክት፦ አጭበርባሪዎች ቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከቢዝነስ አጋር ወይም ከመንግስት መስሪያ ቤት የተላከ በማስመሰል በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ያጭበረብራሉ።
👉በስልክ ጥሪ፦ ከሶስት ማጭበርበሮች መካከል አንዱ በስልክ ጥሪ የሚከሰት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። አጭበርባሪዎች ጥሪዎችን ከባንክ፣ ከቴሌኮም አቅራቢዎች፣ ከህግ አስከባሪዎችና መሰል ተቋማት የደወሉ በማስመሰል ለማታለል ይሞክራሉ።
👉በኢ-ሜይል፦ ከአጭበርባሪዎች የተላኩ ኢሜይሎች እውነተኛ ይመስላሉ፣ ነገር ግን በደንብ ሲመረመሩ ገንዘብዎን ወይም መረጃዎን ለመስረቅ የተነደፉ አደገኛ ሊንኮችና አባሪዎችን ይሆናሉ። በባህሪያቸው አስቸኳይ የሚሉና ከመንግስት ወይም ከህግ አስከባሪ ተቋማት የተላኩ መስለው ይላካሉ።
👉በማህበራዊ ሚዲያ፦ የማህበራዊ ሚዲያዎች ለአጭበርባሪዎች የተመቹ ናቸው። አጭበርባሪዎች ሃሰተኛ አካውንቶችንና ፕሮፋይል በመለጠፍ ጓደኛ፣ ወዳጅና የቅርብ ሰው በመምሰል ያጭበረብራሉ።
👉በድረገጽ፦ አጭበርባሪዎች የታወቁ ካምፓኒዎች ለመምሰል ሃሰተኛ ድረገጾችን ይፈጥራሉ። ከዚህ ባሻገር ታዋቂ ሰዎችን ምስክርነት እንደሰጡ በማስመሰል ለማታለል የሚሞክሩ ሲሆን እርስዎ በድረገጾቹ ላይ እምነት እንዲጥሉ ሃሰተኛ ሪቪው ያስቀምጣሉ።
👉በአካል፦ አንዳንድ ማጭበርበሮች በአካል ይፈጸማሉ። ቤት ለቤት፣ እየተዝናኑ ወይም ታክሲ እየጠበቁ፣ በአደባባዮችና በተለያዩ ቦታዎች ወደ እርስዎ ቀረብ ብለው ለአንድ ‘የበጎ አድራጎት ድርጅት’ መዋጮ እየሰበሰቡ በመምሰል መዋጮ ሊጠይቁዎ ይችላሉ። ከዚህ ባለፈ ግላዊ መረጃዎችዎን ለማግኘት እንዲረዳቸው የዳሰሳ ጥናት እየሰሩ በማስመሰል ፎርም በማስሞላት መረጃዎችን በመመንተፍ ሊያጭበረብሩ ይችላሉ።
የጥንቃቄ መልዕክቶቹ መረጃ የተገኘው ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ነው።