ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ኩባንያ አዲስ የቢዝነስ ቻርተር አውሮፕላን ተቀበለ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቦይንግ ኩባንያ የቢዝነስ ቻርተር አውሮፕላን ተረክቧል።

በመረሃ ግብሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ሃላፊ ለማ ያዴቻ ፣የቦይንግ ኩባንያ ተወካዮችና የአየር መንገዱ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት፥ ይህ አዲስ አውሮፕላን አየር መንገዱ በአፍሪካ የያዘውን የመሪነት ድርሻ በማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማስቀጠል አንድ እርምጃ የሚያሻግረው ነው ብለዋል።

አየር መንገዱ ዛሬ የተረከበው B737-800 የተሰኘ የቻርተር አውሮፕላን ለቢዝነስ ስራዎች፣ለመሪዎች እና ለየት ላሉ አገልግሎት እንደሚውልም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጣይም የአገልግሎት አድማሱን የማስፋፋት ሂደቱ ተመሳሳይ የቻርተር አውሮፕላኖችን ወደ ገበያው እንደሚያስገባ ገልጸዋል።

አየር መንገዱ ያነገበው የራዕይ 2035 ግቡን ለማሳካትም የላቀ አገልግሎትን ተቀዳሚ ያደረገ ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም