ቀጥታ፡

በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኢፍጣር መርሀ-ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2017(ኢዜአ)፦ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊም ዳያስፖራ ማህበረሰብ የረመዳንን ጾም ምክንያት በማድረግ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኢፍጣር መርሀ-ግብር ተካሄደ።

በዝግጅቱ ላይ በአሜሪካ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብናልፍ አንዱአለም በኤምባሲው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ውስጥ የኢፍጣር ኘሮግራም ሲካሄድ በየቤቱ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም በጋራ እየተሰባሰበ ፍቅሩን መግለፅ በእጅጉ የተለመደ ባህል መሆኑን አስታውሰዋል።

ለዘመናት ጠብቀነው የኖርነውን የአብሮነት እሴታችንን የሚሸረሽሩ አስተሳሰብና ተግባራትን በማስተካከል ለትውልዶች ለማስተላለፍ ሁላችንም በጋራ ተግተን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

በሰሜን አሜሪካ የሚኖረው የሙስሊም ማህበረሰብ ከዚህ ቀደም ለነበሩ ልዩ ልዩ አገራዊ ጥሪዎች ለሰጡት አዎንታዊ ምላሽ በተለይም ለበድር ኢትዮጵያ፣ ፈርስት ሄጂራ እና ሰላም ፋውንዴሽን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


 

በፕሮግራሙ ላይ የፈርስት ሂጂራ ተወካይ ኡስታዝ መሀመድ ደጉ፣ የበድር ኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ወርቁ፣ የአባይ ንጉሶችና የሰላም ፋውንዴሽን ተወካይ ኡስታዝ ጀማል፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊው የኮሎራዶ ግዛት ምክር ቤት አባል አምሳሉ ካሳውና በአሜሪካ የሱዳን አምባሳደር መሀመድ አብደላ እድሪስ የአብሮነት መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

በኤምባሲው በዝግጅቱ ላይ የጎረቤት ሀገራት አምባሳደሮች፣ የሙስሊም አደረጃጀት አመራሮች፣ በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊም ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት መገኘታቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም