ቀጥታ፡

የአፋር እና የሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የጋራ የኢፍጣር መርሃ ግብር ዛሬ ማምሻውን በሰመራ ይካሄዳል

ሰመራ፤መጋቢት 8/2017(ኢዜአ)፦የአፋር እና የሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣የሀይማኖት አባቶች የአገር ሽማግሌዎች የሚሳተፉበት የኢፍጣር መርሃ ግብር ሰመራ ከተማ ዛሬ ማምሻውን ይካሄዳል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ለመታደም የሱማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ማሀመድ፣ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሰመራ ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የሰላም ሚኒስትር መሀመድ ኢድሪስ እና ሌሎች የፌዴራል መንግስት አመራሮች፣የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ እና ሌሎችም አመራሮች ሰመራ ገብተዋል።

የኢፍጣር ተጋባዦቹን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባ፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የመርሃ ግብሩ ዋነኛ ዓላማ በታላቁ የረመዳን ወር በሁለቱ ክልሎች ህዝቦች መካከል አብሮነትን ይበልጥ ለማጠናከር መሆኑ ታውቋል።

በተመሳሳይ የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድርን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የኃይማኖት አባቶች የተሳተፉበት የኢፍጣር ፕሮግራም መጋቢት 01 ቀን 2017 ዓ.ም በጅግጅጋ መካሄዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም